ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ

982

ህዳር 16 / 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ፓኪስታን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ የሚያስከትለውን ችግር ለመከላከል በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡

በፓኪስታን የኢትየጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቢልዋል ቡቶ ዛርዳሪ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

የሀገራቱን ሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ቀጣናዊና ዘርፈ ብዙ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት እየተሰራ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ልምድ ለፓኪስታን ለማጋራት እንደሚሰራም አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡

የፓኪስታን ባለሃብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸውን የንግድ ዘርፎች ያብራሩት አምባሳደር ጀማል ፓኪስታን ቡና፣ ሻይ፣ የቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ከኢትዮጵያ ማስገባት እንደምትችል ገልጸውላቸዋል።

በአንጻሩ ፓኪስታን የህክምና፣ የኮንስትራክሽን፣ የጨርቃ-ጨርቅ፣ የስኳርና የመድሃኒት ውጤቶችን ወደ ኢትዮጵያ መላክ እንደምትችል በመጠቆም፡፡

አምባሳደር ጀማል የኢትዮጵያ መንግስት ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የጎርፍ አደጋ፣ የምግብ ደህንነት ችግሮችን በተመለከተም ከፓኪስታን መንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ፓኪስታን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ተፅእኖዎችን በመቃወም ላሳየችው አጋርነትም አምባሳደሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፓኪስታን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቢልዋል ቡቶ ዛርዳሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ችግር በገጠማት ወቅት ኢትዮጵያ ላሳየችው አጋርነት አመስግነዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ በፓኪስታን ኤምባሲዋን መክፈቷ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ባለብዙ ወገን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መልካም ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል የሚደረገው ቀጥታ በረራ በፓኪስታንና በአፍሪካ መካከል ያለውን ትብብር በማሳደጉ በኩል አዲስ የትብብር ምዕራፍ ይፈጥራል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም