በኢትዮጵያ በማህበረሰቡ ላይ ስጋት እየሆነ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

422

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 16 /2015 በኢትዮጵያ በማህበረሰቡ ላይ ስጋት እየሆነ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ የፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን  የጸረ- ሙስና ቀን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በዓሉ  ሕዳር 30 ቀን 2015 ዓ ም "ሙስናን መታገል በተግባር" በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተጠቁሟል።

የፌደራል የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤  ኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል የተቀመጡ ዓለማቀፍ ስምምነቶች ፈርማለች።

የፈረመቻቸው ዓለማቀፍ ሕጎችን ተግባራዊ በማድረግም በረቀቀ ሁኔታ የሚፈፀመውን ድንበር ተሻጋሪ የሙስና ወንጀል ለመከላከል ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራች ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የሙስና ወንጀል በአገር ኢኮኖሚና በሕዝቦች ማሕበራዊ ሂወት ላይ እያደረሰ ያለውን ፈተና በብቃት ለመወጣትም በየደረጃው በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

ኮሚሽኑ በ2013 ዓም ባካሔደው ጥናት ሙስና በማህበረሰቡ ላይ ስጋት እየሆነ መምጣቱን መረጃዎች የሚያሳዩ በመሆኑ በተጠናከረ አግባብ መታገል እንደሚገባም ነው ያመላከቱት ።

በሙስና የሚፈፀም ወንጀል የህብረተሰቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ጥያቄ ውስጥ በመክተት በመንግስትና በህዝብ መካከል አለመተማመንን የሚፈጥር መሆኑንም  ገልፀዋል።

ሙስና ዜጎችን ለስደት ለእንግልትና ለድህነት የሚዳርግ በመሆኑም ሁሉም አካላት በጋራ ሊከላከሉት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

ህብረተሰቡም የትኛውም የሙስና ተግባራት ሲመለከት በነጻ የስልክ መስመር በ9555  ጥቆማ በመስጠት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣም ነው በዚሁ ወቅት ጥሪ የቀረበው።

በዓሉ ሕዳር 30 ቀን 2015 ዓ ም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት በድምቀት እንደሚከበርም ተገልጿል።

መንግሥት በጥናት በደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ መገለጹ የሚታወስ ነው።

በሙስና ላይ የሚደረገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙም ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም