ቀጥታ፡

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮችን በስፋት ተደራሽ የሚያደርግ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት ይገባል-ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሮችን በስፋት ተደራሽ የሚያደርግ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በግብርና ኮሜርሻላይዜሽን እንዲሁም የኩታ ገጠም እርሻን የሚመለከት የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ በግብርና ምርታማነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ በመወያያት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን መጠቆም ነው፡፡

በመድረኩ የግብርና ኮሜርሻላይዜሽንን በሚመለከት ሳይንሳዊ ማብራሪያ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ የግብርና ዘርፉን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚከናወኑ ስራዎች ከፋይናንስ ተደራሽነት ጋር ሊተሳሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ አርሶ አደሮች የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ የፋይናንስ ችግሮቻቸው ሊፈቱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ ተቋማት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ ብድርን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ለአርሶ አደሮች በስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የግብርና ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ በማስገባት እንዲሁም ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በቀላሉ ለአርሶ አደሩ በማድረስ ረገድ የሚያበረታታ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለው ኩታ ገጠም የአመራረት ዘዴ ምርታማነትን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡

የኩታ ገጠም እርሻ በአገር አቀፍ ደረጃ ግብርና መካናይዜሽንን ለማስፋት እድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ስንዴን ጨምሮ በሌሎች ምርቶች ራስን ከመቻል ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተጀመረው ውጥን እውን እንደሚሆን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም