ተወላጆቹ በ5 ሚሊዮን ብር በጎንደር ከተማ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት አስጀመሩ

74

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 16/2015 አዲስ አበባ የሚኖሩ የጎንደር ተወላጆች በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ረዳት ለሌላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች በጎንደር ከተማ የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀምረዋል።

የተወላጆቹ ተወካይ አቶ መላክ አየነው በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ "ለወገኖቻችን ችግር ደራሽ እኛው ወገኖች ነን" ብለዋል።

"በተለይም ያሳደገንና ያስተማረንን ማህበረሰብ ለችግሩ ደርሰንለት በመደገፍ ማህበራዊ ሃላፊነታችንን መወጣት ግዴታችን ነው" ያሉት።

ዛሬ የተጀመሩት የቤት እድሳት ቀጣይነት ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ መላክ፤ በመጀመሪያው ዙር የ6 አቅመ ደካሞችን ቤት በ5 ሚሊዮን ውጪ በመገንባትና ሙሉ የቤት እቃ ጭምር በማሟላት ነዋሪዎቹን የቤት ባለቤት እናደርጋለን ብለዋል።

''በሁለተኛው ምእራፍ ደግሞ የ5 አቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ የእድሳት ስራ በማከናወን ችግረኛ ወገኖችን ለመደገፍ እኛ የአካባቢው ተወላጆቹ ዝግጁ ነን'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው በሰጡት አስተያየት "ወቅቱ ያለው የሌለውን በሚችለው አቅም ሁሉ የሚያግዝበትና የሚደግፍበት ጊዜ ነው"።

በተለይም አቅመ ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች የመኖሪያ ቤት በማደስና በሚቻለው አቅም እንደገና በመስራት በጎ ተግባር መፈፀም ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህም ባለፈው ክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በከተማው የተለያዩ ቀበሌዎች የ152 አቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች እድሳት በማድረግ የነዋሪዎችን ማህበራዊ ችግር ለመፍታት ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።

በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች እንደሚገኙ ጠቁመው፤ እነዚህን ወገኖች ለማገዝ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጎንደር ተወላጆች በራሳቸው ተነሳሽነት የፈፀሙት ተግባር ሌሎችም ሊወስዱት የሚገባ ልምድ መሆኑን ገልፀዋል።

በከተማዋ በመጭው ጥር ወር በድምቀት የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ለመታደም የሚመጡ ዳያስፖራዎችም በዓሉን ከማክበር በዘለለ ማህበራዊ ችግሮችን በሚያቃልሉ የልማት ስራዎች በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲሳርፉ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

''በክረምት ከዝናብ ውሃ በበጋ ደግሞ ከፀሐይ ብርሃን ማዳን በማይችል ደሳሳ ቤት ውስጥ ረጅም ጊዜ በችግር ውስጥ ሆኜ አሳልፌያለሁ'' ያሉት ደግሞ የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ አበራ ሰፊው ናቸው፡፡

ዛሬ ላይ ቤቴ በአዲስ ታድሶ እንዲሰጠኝ ስራ በመጀመሩ በእጅጉ ተደስቻለሁ ለዚህ እድል ላበቁኝ ሁሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ ተጠቃሚ ወይዘሮ ፈንታነሽ ደሴ በበኩላቸው ''ክረምቱን ዝናብ በላዬ ላይ እየፈሰሰ እንቅልፍ አጥቼ አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፌአለሁ'' ብለዋል፡፡

እድሉን በማግኘቴ እጅግ ተደስቻለሁ፤ ይህን መልካም ተግባር ለሚፈጽሙት ሁሉ ውለታቸውን ፈጣሪ ይክፈላቸው ሲሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቤት እድሳት ማስጀመር ስነ-ስርአቱ የከተማው አመራሮችን ጨምሮ ነዋሪዎችና በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጎንደር ተወላጆች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም