ኔፓድ ኢትዮጵያን በፈጠራና የወጣቶች የስራ ዕድል ዘርፎች ለማገዝ ፍላጎቱን ገለጸ

147

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 16 / 2015 በአፍሪካ ልማት አጋርነት (ኔፓድ) የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ (ኤዩዳ-ኔፓድ) ኢትዮጵያን በፈጠራና በወጣቶች የስራ ዕድል ለማገዝ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኒያሚ ኒጀር በመካሄድ ላይ ከሚገኘው 17ኛው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ጉባኤ ጎን ለጎን በኔፓድ የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም አህጉራዊ ተቋሙ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ለሚገኘው የልማት ስራዎች ስኬታማነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኤጀንሲው ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ ገልጸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የወጣቶች የስራ እድል እና የፈጠራ ዘርፎችን ለማገዝ ያለውን ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለዋና ስራ አስፈጻሚዋ በኢትዮጵያ የስራ አጥነትን ለመቀነስ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ለማሳደግ ስለተከናወኑ ስራዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሁለቱ አካላት በመጪው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በተለይ በስንዴ ልማት እንዲሁም በቴክኖሎጂና በሳይንስ ሙዚየም የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶች በተመለከተ ገለጻ ለማቅረብ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

በኔፓድ የአፍሪካ ልማት ኤጀንሲ በአፍሪካ አህጉራዊ ትስስር እንዲፋጠርና አጅንዳ 2063 ስኬታማ እንዲሆን በአህጉርና በቀጠና ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የልማት ፕሮጀክቶች የሚያስተባብርና ለተፈጻሚነታቸው ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም