የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ውይይት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክር ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15 ቀን 2015 (ኢዜአ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረ-መስቀል ጫላ በኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከርና እና በቀጣይ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ በሀገራት መካካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እያደገ የመጣ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱ በውይይቱ ተነስቷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ የረጅም ጊዜ የንግድ እና ኢኮኖሚ ትስስር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ይበልጥ ለመስራት ፍላጎት ያለ መሆኑን ጠቁመው ነባሩን የንግድ ስምምነት ገምግሞ ወደ ሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነት ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ መከወን አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የንግድ ትስስሩን አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲያግዝ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚና የመንግስት ሙያተኞች አቅም በመገንባት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማመቻቸት፣ ተሞከሮንና ልምድን በማጋራት፣ የነጻ ገበያ አሰራርና የመደራደር አቅምን ለማሻሻል የአቅም ግንባታ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡
አምባሳደር ካንግ ሲዮክ ሂ በበኩላቸው በቀጣይ የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ እንዲመቻችላቸውና ከሰፊው ገበያ ተጠቅመው ኢትዮጵያንም መጥቀም እንዲችሉ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈራረም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በ2030 የዓለም ኤክስፖን ለማዘጋጀት ሀገራቸው በውድድር ላይ መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ ውድድሩን ለማሸነፍ የኢትዮጵያ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት መጠየቃቸውን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡