መንግስት የጀመረውን የፀረ ሙስና ትግል በማገዝ ትውልዱን በመልካም ስነ-ምግባር ኮትኩቶ ለማነፅ የድርሻችንን እንወጣለን- የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የጀመረውን የፀረ ሙስና ትግል በማገዝ ትውልዱን በመልካም ስነ-ምግባር ኮትኩቶ ለማነፅ የድርሻችንን እንወጣለን- የሃይማኖት አባቶች
ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 15/2015 መንግስት የጀመረውን የፀረ ሙስና ትግል በማገዝ ትውልዱን በመልካም ስነ-ምግባር ለመኮትኮት የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ በጎንደር ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች ተናገሩ፡፡
የሃይማኖት መሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሙስና የሀገር እድገት እንቅፋት በመሆኑ የእምነት ተቋማቱ በማህበረሰብ የሰብእና ግንባታ ላይ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መምህር መላከ ቆሞስ አባ ገብረእግዚአብሄር ደምሴ እንደተናገሩት፤ መልካም ስነ-ምግባር የተላበሰ ዜጋ በመፍጠር ረገድ ቤተ-ክርስቲያን ታላቅ ሃላፊነት አለባት፡፡
በሀገራችን የሚስተዋለው የሙስና ድርጊት ለግል ጥቅም በቆሙ ነውረኞች የሚፈጸም እኩይ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
መንግስት በሙስና ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ጠቁመው፤ የሰው ልጅ ለፍቶ ጥሮና ግሮ እንዲበላ እንጂ በአቋራጭ እንዲበለጽግ ሃይማኖቱ አይፈቅድም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ቤተ እምነቶች ሙስናን ከማውገዝ ባለፈ ህጻናት መልካም ስብእና ተላብሰው እንዲያድጉ ማስተማር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንም ሙስናን የሚጠየፍ ትውልድ በመቅረጽ በኩል የድርሻዋን ትወጣለች ብለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ሀጂ አደም አህመድ በበኩላቸው ሙስና መንግስትን የፈተነ የሀገር እድገትና የልማት ጸር ነው ብለዋል፡፡
ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አጥብቆ ከሚከለክላቸው መንፈሳዊ ትእዛዛት መካከል ሙስና አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ሃጂ አደም፤ ሀገርና ትውልድ ገዳይ በመሆኑ መንግስት ትኩረት መስጠቱ ተገቢና ወቅታዊ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የእምነት ተቋማት ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባር በማነጽ ዜጎች በሰሩትና በለፉት ልክ ብቻ እንዲያገኙና ሀገርን በታማኝነት እንዲያገለግሉ አጥብቆ በማስተማር ሃይማኖታዊ ሃላፊነታችን እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
''የሙስናን ችግር ከሃይማኖታዊ አስተምሮ ጋር በማያያዝ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በሚያስችሉ ተግባራት ዙሪያ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት የልማት ፎረም ተወካይ ወንደሰን ሽፈራው ናቸው፡፡
ፎረሙ ከሃይማኖት መሪዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በሰላም ግንባታ ዙሪያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጎን ለጎን ሙስናን ለመከላከል በሚያግዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም የህብረሰቡን ሞራልና ስነ-ምግባር በሚገነቡ ማህበራዊ እሴቶች ዙሪያ የግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ህዳር 08 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል።