በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በማደራጀት አለም አቀፍ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

254

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 በኢትዮጵያ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን በማደራጀት አለማቀፍ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ ህግ ዙሪያ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በሚፈጥሩ ፖሊሲዎች፣ ንግድን በሚያሳልጡ አቅርቦቶች፣ መሰረተ-ልማቶች እና አገልግሎቶች የተደገፈ እንዲሁም የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና ልዩ ማበረታቻዎችን የያዘ ነው።

የኢኮኖሚ ዞኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ነፃ የንግድና ሎጂስቲክስ ቀጣናዎች፣ የሳይንስና የአገልግሎት ፓርኮች፣ የግብርናና እንስሳትና ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን ሁሉንም ወይንም አንዱን ይዞ የሚደራጅ የተለየ አካባቢ መሆኑ ረቂቅ አዋጁ ያትታል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ኮሪደር ለማድረግ  የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ  ቆይተዋል።

ከነዚህ መካከል በመንግስት አስራ ሶስት፣ በግል ስድስት፣ በክልሎች ደግሞ ሶስት በማኒፋክቸሪንግና ላኪነት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በመዘጋጀት ላይ ያለው የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አሰራር ይበልጥ በማሻሻል ኢትዮጵያ ቀጣናዊ እና አለም አቀፋዊ የንግድና የኢንቨስትመንት ተሳትፎዋ እንዲያድግ ያግዛል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የንግድ ቀጣና ውስጥም የድርሻዋን እንድታገኝም ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ረቂቁ ህግ ፀድቆ ወደ ስራ ሲገባ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የንግድ ኮሪደሮች እንዲቋቋሙ በማድረግ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባሻገር ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል፡፡

ህጉ የግል ባለሃብቶችን ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ አህጉራዊና ቀጣናዊ የንግድ ትስስሮችን ማሳደግ አንዱ አላማ መሆኑን አብራርተዋል።

የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም