ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለሚያከናውኑ ተመራማሪዎች የማበረታቻ ስርዓት ተዘርግቷል-የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ

177

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 15/2015 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለሚያከናውኑ ተመራማሪዎች የማበረታቻ ስርዓት በመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

በ1942 ዓ.ም 33 ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ላይ በ14  ካምፓሶች 70 የቅድመ ምረቃ እና 293 የድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል።

ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ይህ አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎቶች ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ በርካታ ማሻሻያዎችን እያደረገ ስለመሆኑም ነው የሚገልጸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ እንደሚሉት፤  ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ የጥናት መፅሔሄቶች ላይ የሚያሳትማቸውን ጥናትና ምርምር ውጤቶችን ብዛት እያሳደገ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለማስፋት የምርምር ፈንድ ስርዓት በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፈንዱ በዋናነት ለምርመር ስራዎች የሚውል ፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ተመራማሪዎች ከዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለዩኒቨርሲተው ከሚያስገኙት ገቢ አራት በመቶውን ለራሳቸው የሚወስዱበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በታወቁ የዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ የምርምር ስራዎችን ለሚያሳትሙ ተመራማሪዎች እስከ 25 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ማበረታቻ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በዚህም በዩኒቨርሲቲው በርካታ የምርምር ስራዎች እየወጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት ከ 2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የምርምር ስራዎች በጆርናሎች ላይ ታትመው ወጥተዋል ነው ያሉት፡፡

የምርምር ውጤቶችም ለፖሊሲ ግብአት እንዲውሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጸት፡፡

ተመራማሪዎች ለምርምር ከሚያመጧቸው ቁሳቁሶች ጀምሮ ለምርምር የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች በርካታ የምርምር ስራ ላሳተሙ ተመራማሪዎች  እውቅናና የገንዘብ ሽልማት መስጠቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም