ስምንት ማዕከላት ተጠግነው ለህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስ መቻሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ስምንት ማዕከላት ተጠግነው ለህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስ መቻሉ ተገለጸ
ወልዲያ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 በነበረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸው ስምንት ማዕከላትን ፈጥኖ በመጠገን ለህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዳረስ መቻሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወልዲያ ዲስትሪክት ገለጸ።
የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል በቅርቡ በፕሪቶሪያ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ተቋርጠው የነበሩ መሰረታዊ አገልግሎቶቹን ለመመለስ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ መቀጠሉን አንዱ ማሳያ መሆኑ ተመልክቷል።
በተገኘው ሰላም የኤሌክትሪክ ኃይል በማግኘታቸው ተዘግቶ የነበረውን ድርጅታቸውን እንደገና ማስጀመር እንደቻሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።
በዲስትሪክቱ የስርጭት፣ ኮንስትራክሽን፣ ትግበራና ጥገና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥጋቡ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዲስትሪክቱ ከሚያስተዳድራቸው 13 ማዕከላት ውስጥ በስምንቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ነበር።
ጉዳቱን በመለየት ለአገልግሎት ለማብቃትም 321 ኪሎ ሜትር መካከለኛና ዝቅተኛ መስመር ጥገና ከመካሄዱም በላይ የወደሙ 46 ትራንስፎርመሮችን የመጠገንና የመተካት ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የመስመር ተሸካሚ "ታወሮች " ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠገን መቻሉን ጠቁመው፤ አጠቃላይ የደረሰው ጉዳት ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ጠቅሰዋል።
የተጠገኑት ማዕከላት የላልይበላ፣ የአይና ቡግና፣ የሮቢት፣ የቆቦ፣ የሰቆጣ፣ የአምደ ወርቅ፣ የዝቋላና ኒሯቅ ከተሞች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የቆቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ገነት አርብሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በነበረው ችግር ምክንያት የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት በመቋረጡ የንግድ ስራቸውን ለማንቀሳቀስ ተቸግረው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም የመብራት አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻሉ የንግድ ድርጅታቸውን እንደገና ከፍተው መስራት መጀመራቸውን አስረድተዋል።
የላልይበላ ከተማ ነዋሪው አቶ ደሳለ ሃዋዝ በበኩላቸው፤ ለአንድ ዓመት አራት ወራት ያህል በከተማው መብራት ባለመኖሩ ኑሮው ሁሉ ፈተና ሆነባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
የሚተዳደርበትን የብረታ ብረትና የእንጨት ስራ ድርጅት በመብራት ችግር ምክንያት ተዘግቶ መክረሙን ጠቁሞ፤ አሁን በተፈጠረው ሰላም የሃይል አገልግሎት በማግኘቱ ስራውን እንደገና መጀመሩን ገልጿል።
የሐራ፣ ሐሮ፣ ድሬ ሮቃና ጭፍራ ከተሞችን የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ከዲስትሪክቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።