የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘላቂ የጤና ግቦችን ለማሳካትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘላቂ የጤና ግቦችን ለማሳካትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘላቂ የጤና ግቦችን ለማሳካትና የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያግዙ የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱን 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን መደበኛ ቃለ ጉባኤ በመመርመር በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መንግስት መካከል የተደረገውን የ10 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነት ረቂቅ በአዋጅ ቁጥር 1280/2015 ዓ.ም በማድረግ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።
ብድሩ በረጅም ጊዜ እና በአነስተኛ ወለድ የሚመለስ ሲሆን የእናቶችን፣ የህፃናትና ወጣቶችን ጤና በማሻሻል የጤናውን ዘርፉ የልማት ግብ ለማሳካት እንደሚውል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር የደረሰውን የብድር ስምምነት ረቀቅ በአዋጅ ቁጥር 1281/2015 ዓ.ም በማድረግ በ1 ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በ181 ወረዳዎች የሚተገበረው የብድር ስምምነት በ400 ሚሊየን ዶላር 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎችን በቀጥታ በተዘዋዋሪ ደግሞ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።
የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ ከጣሊያን መንግስት የተገኘው የ10 ሚሊየን ዮሮ ብድር ለማህበረሰብ ጤና አጠባበቅ ተግባር የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።
የብድር ስምምነቱ ወደ ተግባር ሲሸጋገርም የእናቶች፣ የህፃናትና የወጣቶችን ጤና ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት የተገኘው የገንዘብ ብድር የህብረተሰቡን ጤና በሚያሻሽሉ ተግባራት ላይ እንዲውል ተገቢው ክትትልና ድጋፍ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከጣሊያን መንግስት የተገኘው የብድር ሰምምነትም የሁለቱን አገራት በትብብር ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር የተደረገው የብድር ስምምነት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚውል ተናግረዋል።
ስምምነቱ በ181 ወረዳዎች የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰው፤ የአርሶና አርብቶ አደሩን ገቢ በማሳደግ፣ ድህነትን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የተገኘው ብድር ኢትዮጵያ የያዘችውን የግብርና ምርታማነት አጠናክራ ለማስቀጠል እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የብድር ስምምነቶቹ የጤና ልማት ስራዎችን ለማሻሻልና የበጋ መስኖ ስራዎችን በመደገፍ ምርታማነትን በማሳደግ ለስራ እድል ፈጠራና በምግብ እራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል።