መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም ሊደግፍ ይገባል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ሁሉም ሊደግፍ ይገባል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
ሕዳር 15/2015(ኢዜአ) መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ኢትዮጵያውያን እንዲደግፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊዋ ዶክተር ራሔል ባፌ እና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሷል።
ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የፌደራል መንግስትና ህወሃት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የደረሱት የሰላም ስምምነት ትልቅ እርምጃ ነውም ብለዋል።
ሁለቱ ወገኖች ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም መስማማታቸው የኢትዮጵያን ሰላም ለማጽናት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ያነሱት አመራሮቹ በተቀመጠው የአፈጻጸም የጊዜ መርሃ ግብር ለመተግበርም በቅንነትና በትብብር መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በግጭት ቀጠናው ውስጥ የነበሩ ወገኖች ያገኙትን የሰላም ተስፋ ዘላቂ ከማድረግ ጎን ለጎን፤ ተገቢውን ድጋፍና መልሶ ማቋቋም እንዲደረግላቸው በትኩረት መስራት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ አክለውም በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጠቂ የሆኑ የአማራ፣ የአፋርና የትግራይ ወገኖችን በፍትሐዊነት ማቋቋምና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
መንግስት ከሰላም ስምምነቱ ማግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ተገቢና የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የባንክ እና ሌሎች አገልግሎቶች ስራ እንዲጀምሩ እያካሄደ የሚገኘው የመልሶ ግንባታ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የገለጹት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ መንግስት እያካሄደ ያለውን ዘርፈ ብዙ የመልሶ ማቋቋም እንቅሰቃሴ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን ከጎኑ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እንዲረባረቡም ጥሪ አቅርበዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቆየው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የፌደራል መንግስት እና ህወሃት ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ መፈራረማቸው ይታወሳል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የህወሃት ታጣቂ አመራሮች በኬኒያ ናይሮቢ ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም የስምምነቱ ዝርዝር የአፈጻጸም ሂደት ላይ ተስማምተዋል።