ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት የሚያስችለውን ስራ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.አ.አ. በ2035 25 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማስገባት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ለዚህም የበረራ መዳረሻውንና የአውሮፕላን ቁጥሩን በእጥፍ በማሳደግ 65 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን እና 3 ሚሊዮን ቶን ጭነት ለማጓጓዝ አልሞ እየሰራ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ አየር መንገዱ መዳረሻውንና የአውሮፕላን ቁጥሩን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ ያለው እ.አ.አ. በ2035 ራዕዩን ለማሳካት በያዘው ዕቅድ መሰረት መሆኑን ጠቁመዋል።

የአየር መንገዱ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዋና ዓላማ በኢንዱስትሪው ውስጥ የያዘውን አስተማማኝ የዕድገት ጎዳና ማስቀጠል ብሎም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር መሆኑንም ተናግረዋል።

አየር መንገዱ በ2035 ራዕዩ የበረራ መዳረሻውን በእጥፍ ለማሳደግ በማቀድ አሁን ያለውን 131 መዳረሻ ወደ 207 የማሳደግ ትልም ሰንቋል ብለዋል።

የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካትም አሁን ያሉትን 140 አውሮፕላኖች ወደ 271 ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የተገበረውን ራዕይ በ2025 ጊዜው ከማብቃቱ ቀድሞ ማሳካቱን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አዲሱ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣንና በትርፍ የታጀበ ዕድገት ማስቀጠል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከመመስረቱ በፊት ጀምሮ የአፍሪካ አገራትን ሲያገናኝ የነበረና አሁንም አጠናክሮ የቀጠለ የፓን አፍሪካ አየር መንገድ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

“ለአህጉሪቱ ልማት መጠናከር አፍሪካውያንን ማቀራረብ የሚለው ሀሳብ ለአየር መንገዱ የተሰጠ ተልዕኮ አድርገን እንመለከተዋለን” ሲሉም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የራሳቸውን አየር መንገድ ለመሰረቱ አገራት የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የአህጉሪቱ አየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ እንዲጎለብት የመሪነት ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ገልጸዋል።

“ከዚህ አንጻር ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው በሎሜ ቶጎ የበረራ ማዕከል ያለውና በምዕራብ አፍሪካ አገራት አገልግሎት ለመስጠት ከ12 ዓመታት በፊት የተመሰረተው ‘አስካይ አየር መንገድ’ ነው።

‘አስካይ አየር መንገድ’ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ 25 መዳረሻዎች ያሉትና አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት በመስጠት ትርፋማ የሆነ ኩባንያ ለመሆን በቅቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ኩባንያ በማስተዳደር ላይ ያለ ከመሆኑም በተጨማሪ 27 በመቶ የአክሲዮን ባለቤት ነው” ብለዋል።

ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማላዊ መንግሥት ጋር በገባው ሽርክና መሰረት የአገሪቱን አየር መንገድ 49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፤ ኩባንያውን እያስተዳደረ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሆን የማላዊው አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሽርክና ለመፍጠር የሚያስችለውን ስምምነት በቅርቡ የተፈራረመ መሆኑንም አቶ መስፍን ጠቅሰዋል።

ሥራ ለመጀመርም ቅድመ ዝግጅት ያጠናቀቀ ሲሆን ወደ ተግባር ለመግባትም ከአገሪቱ መንግሥት ይሁንታን እየጠበቀ ነው ብለዋል።

“በቅርቡ የናይጄሪያን ብሔራዊ አየር መንገድ ‘ናይጄሪያ ኤር’ ለመመስረት ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉም ጠቁመዋል።

በስምምነቱ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ሲሆን አፍሪካ ውስጥ አገር በቀል የሆኑ አየር መንገዶች የሚፈጠሩበትን መንገድ ለማበረታታት በአህጉሪቱ የዚህ ዓይነቱ የትብብር ግንኙነት እንዲመሰረት የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ለማድረግ የዚህ ዓይነቱ የጋራ ትብብርን የመመስረት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አህጉር በሁሉም ረገድ የተዋጣለትና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለ ኩባንያ ሲሆን በዚህም በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኘ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም