ኢትዮጵያ ለኬኒያ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ መጀመሯ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ጥሩ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለኬኒያ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ መጀመሯ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ጥሩ መሰረት የሚጥል መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 ኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ለኬኒያ የኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብ መጀመሯ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ጥሩ መሰረት የሚጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ገለጸ።
የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የሃይል ማስተላለፊያ መስመር እንዲሁም ኮንቨርተር ጣብያን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች ጎብኝተዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስፈጻሚ ክብሮም ካህሳይ፤ ከኬኒያ ጋር በተፈረመው የውል ስምምነት መሰረት የኤሌክትሪክ ሽያጭ መጀመሩን ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሰረት ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት 200 ሜጋ ዋት ሃይል ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ አቅርቦቱ ወደ 400 ሜጋ ዋት ከፍ ይላል ብለዋል።
አሁን ላይ በሙከራ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ መደበኛ የሃይል ማስተላለፍ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።
በአጠቃላይ መስመሩ 2 ሺህ ሜጋ ዋት ሃይል የማስተላለፍ አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ከኬንያ ባለፈ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያን ጨምሮ ከሌሎች አፍሪካ አገራት ጋር በኢኮኖሚ ለመተሳሰር በሚደረገው ጥረት ትርጉም ይኖረዋል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው እንደ አገር ከጎረቤት አገራት ጋር በኢኮኖሚ ለመዋሃድ ለተጀመረው ጥረት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኢትዮ-ኬኒያ ፕሮጀክት የወላይታ ዞን ኮንቨርተር ጣብያ የኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊ ሀብታሙ ግርማ፤ የፕሮጀክቱ እውን መሆን የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር ጣቢያው ባለበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችም ገቢራዊ ማድረግ በፕሮጀክቱ ከተያዙ ዕቅዶች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮ-ኬንያ ፕሮጀክት ሳይት ስራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አያሌው፤ ፕሮጀክቱ በዓይነቱ የመጀመሪያውና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለበት ሜጋ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ለሚሰሩ መሰል የልማት ስራዎች ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የሃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በአጠቃላይ 1 ሺህ 46 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 994 ከፍተኛ የሃይል ተሸካሚ ማማዎች ያሉት መሆኑ ታውቋል።