መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረገ ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር/2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄፍሬ ኤንያማ ጋር በኒያሚ በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በኒያሚ በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት 17ኛ ልዩ ስብሰባ እየተሳተፉ ያሉት አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በፕሪቶሪያ ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ለሚኒስትሩ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት እንዳለውና መንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስረድተው ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች ብለዋል።
የሰብአዊ ድጋፍና ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጠቀሱት አቶ ደመቀ የዳግም ግንባታና የመልሶ መቋቋም ተግባር ሌላው ትኩረት መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ወቅት ናይጄሪያ በመርህ ላይ የተመሰረተ የማይዋዥቅ አቋም በማራመዷ አቶ ደመቀ ምስጋናቸውን ገልፀዋል፡፡
የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝደንት ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር እንዴት ራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ አሳይተዋል ያሉት አቶ ደመቀ እንደ አንጋፋ መሪም ከሌሎች ጋር በመሆን ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ በመፈረሙ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ውጤቱ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት ብቃት እንዳላት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የናይጄሪያ መንግስት ለስምምነቱ ስኬታማ አፈፃፀም የሚቻለውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አየር መንገድ እንደሆነም የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መጥቀሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው 28 በመቶው የሚሆነውን የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር በያዙት ኢትዮጵያና ናይጄሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ወዳጅነትና ስትራተጂካዊ የባለብዙ ወገን ትብብር እንዲጠናከር በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በኒጀር ርዕሰመዲና ኒያሚ ዛሬ በተጀመረው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ልዩ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያን የልኡካን ቡድን በመምራት እየተሳተፉ ነው፡፡