ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚያደርገው በሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባው በአራት አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ተገለጸ።

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የሚቀርብለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን እንደሚያጸድቅ ተገልጿል።

በተመሳሳይ ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም በሚያቀርበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን ተወያያቶ እንደሚያጸድቅ ተመላክቷል።

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢፌዴሪ መንግስት እና በጣሊያን ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን እንደሚያጸድቅ ተጠቅሷል።

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢፌዴሪ መንግስት እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን እንደሚያጸድቅም ከምክር ቤቱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም