በዞኑ የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ደብረ ብርሀን (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 በሰሜን ሸዋ ዞን የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መመሪያ አስታወቀ።

የአካል ጉዳተኞች ቀን "አካታች የፈጠራ ሥራና ሽግግራዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ቃል ዛሬ በደብረ ብርሀን ከተማ ተከብሯል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ መመሪያ ሀላፊ ወይዘሮ የሮምነሽ ጋሻውጠና እንደገለጹት፣ በአመለካከት ችግር ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተገድቦ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት መብቶቻቸው እንዲከበሩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የክህሎት ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲካተቱ መደረጉን አስረድተዋል።

"በሰሜን ሸዋ ዞን ከ300 ሺህ በላይ አካል ጉደተኞች እንዳሉ ያመለከቱት ወይዘሮ የሮምነሽ፣ በፖለቲካም ተሳትፏቸው እንዲያድግ የዞኑ አስተዳደር በትኩረት እየሰራ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ዓመት በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች 2ሺህ 682 የአካል ጉዳተኛ ቤቶች በአዲስና በጥገና ተሰርተው ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ጥረት መደረጉንም አመልክተዋል።

ከቼሻየር ኢትዮጵያ እና ከደሴ የአካል ተሀድሶ ማዕከል ጋር በመተባበር ለ32 አካል ጉዳተኞች የዊልቸር እና ሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ መለገሱንም ሃላፊዋ ገልጸዋል።

በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ዕድል እዲያገኙም እየተደረገ ነው ብለዋል።

ይሁንና ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ባቂ ባለመሆኑ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፈዴሬሽን ሰብሳቢ አቶ ጌታሰው ፋንታሁን በበኩላቸው፣ ማህበረሰቡ ስለአካል ጉዳተኞች ያለው ግንዛቤ በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

የዞኑ አስተዳደር የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶችን ከመክፈት ባለፈ አካል ጉዳተኞች በዩኒቨርሲቲዎች እስከ 2ኛ ዲግሪ እንዲማሩ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

"ከእዚህ በተጨማሪ አካል ጉዳተኞች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡና የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉ መልካም ጅምሮች ናቸው" ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ያለማክበር ሁኔታ ይስተዋላል ያሉት አቶ ጌታሰው፣ በየደረጃው ችግሩ እንዲስተካከል በማህበሩ በኩል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም