የአፋር ክልል ከተሞች ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተማራጭ እንዲሆኑ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልል ከተሞች ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተማራጭ እንዲሆኑ መስራት ይገባል
ሠመራ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 የአፋር ክልል ከተሞችን በመሪ የዕድገት ፕላን በመምራት ለኑሮ ምቹና ለኢንቨስትመንት ተማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የከተማና የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።
በሰመራ-ሎግያና ዱብቲ ከተሞች አስተዳደሮች የመሰረተ ልማት ግንባታና የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ዛሬ በሰመራ ከተማ የወይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው የሀገሪቱ አብዛኞቹ ከተሞች በመሪ የዕድገት ፕላን ያልተመሠረቱ በመሆናቸው ለተለያዩ የልማትና ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው።
በዚህም ምክንያት የከተሞቹን ዕድገት መቆጣጠር ስላልተቻለ እንደ ውሃና መብራትን ጨምሮ የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መመለስ አስቸጋሪ እየሆነ ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ሠመራን ጨምሮ አብዛኞቹ የአፋር ክልል ከተሞችም ተመሳሳይ ችግሮች እየተጋረጠባቸው እንደሆኑም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት እና የባለሃብቶችን የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች በከተሞች መሪ የዕድገት ፕላን መሰረት መመለስ ይገባል ብለዋል።
ከተሞችን አረንጓዴ፣ ጽዱና ውብ ለኑሮና ለሥራ የተመቹ እንዲሆኑ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም ኢንጂነር ወንድሙ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር እንደ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና ስልክ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች የግንባታና የማስፋፊያ ስራዎችን በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ማከናውን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በየደረጃዉ የሚገኙ አመራሮች ፈጥነው ወደ ስራ በመግባት ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች እየገጠማቸው ካለው ተግዳሮት ትምህርት ወስደው ከወዲሁ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ እንሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል።
የአፋር ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አህመድ ኑር ሳሊም በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የከተሞችን ዕድገት በአግባቡ ለመምራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
እየተከናወኑ ካሉት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል ሰመራን ጨምሮ በክልሉ የከተሞች መሪ የዕድገት ፕላንን በአግባቡ ተግባራዊ የማድረግና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ስራዎቹን እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ወጥነት ባለዉ መልኩ ለማውረድ የበጀትና የአደረጃጀት እንዲሁም የሰዉ ኃይል አቅም ውስንነት ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በማቃለል ለማስወገድ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኢንጂነር አህመድኑር ገልጸዋል።