የአገር ብሔራዊ ስጋት የሆነውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአገር ብሔራዊ ስጋት የሆነውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት የሆነውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲጠናከር የፌደራል የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
በኢትዮጵያ ሙስና መሰረቱን ጥሎ አገልግሎት ለማግኘት እጅ መንሻ እንደ ልማድ እየተቆጠረ መጥቶ ብሔራዊ ስጋት መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።
በመሆኑም የአገር የልማትና የዕድገት ጠንቅ እንዲሁም የሕዝብ የምሬትና እንግልት ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ሙስና ለመዋጋት በቅርቡ የፀረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወቃል።
የኮሚቴውን መቋቋም አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራል ስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የኮሚቴው አባል ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ለትግሉ ውጤታማነት የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የሙስና ሁኔታ ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጥናት መደረጉን ጠቅሰው፤ ችግሩ ብሔራዊ ስጋት መሆኑ ታውቋል ብለዋል።
የሙስና ወንጀል በኢትዮጵያ ከድህነት፣ ከኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት በመቀጠል ከፍተኛ አገራዊ ችግር መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡንም ጠቅስዋል።
በመሆኑም ይህንን የአገር አደጋና ብሔራዊ ስጋት ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት የሕዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲጠናከር ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።
የሙስና ወንጀልን መከላከል የሚቻለው በትውልድ ግንባታ በመሆኑ በስነ-ምግባር ግንባታ ላይ አተኩሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመከላከል ሥራውም የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግሥት የተቋቋመው የፀረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋማትን በማጎልበት ጉድለታቸውን እያረሙ የሙስና ወንጀልን እንዲከላከሉ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
የሙስና ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኮሚቴው ከሕዝቡ ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ከዚህ ቀደም መረጃ በተለያዩ ተቋማት ይሰበሰብ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ሳሙኤል፤ አሁን ላይ ግን በብሔራዊ የመረጃ ቋት እንዲመጣ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የፀረ-ሙስና ትግሉ የአገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ለትግሉ የሁላችንም ትብብርና እገዛ ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።
ተቋማትም ግልፅነት ማስፈን እንዳለባቸውና አመራሮች ተጠያቂነትን ለማስፈን በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸውም ብለዋል።
የመገናኛ ብዙኃንም የፀረ-ሙስና ትግሉን በማገዝ የድርሻቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።