በመስኖ የለማ አዝመራና ያልደረሰ ሰብል በውርጭ እንዳይበላሽ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በመስኖ የለማ አዝመራና ያልደረሰ ሰብል በውርጭ እንዳይበላሽ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 በቀጣይ ቀናት ቅዝቃዜ እና ውርጭ የአየር አዝማሚያ በሚኖራቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች ባልደረሱ ሰብሎች እና በመስኖ አዝመራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያደርስ ጥንቃቄ እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
ኢንስቲትዩቱ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ባሉት አሥር ተከታታይ ቀናት የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አዝማሚያ ትንበያ በተመለከተ ለኢዜአ መግለጫ ልኳል።
በመግለጫውም በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ አየር ሲኖራቸው የሰሜን፣ የሰሜን ምስራቅ፣ የመካከለኛውና ደጋማ አካባቢዎች ቀዝቃዛና ውርጭ የአየር ጸባይ ይኖራቸዋል ብሏል።
የጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ የሐረርጌ ዞኖች ጥቂት ቦታዎች፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ አኙዋ፣ ጌዲዮ፣ ጋሞጎፋ፣ አፍዴር፣ ሊበንና ጎዴ ዞኖች፣ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ክልል ዞኖች ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም እድገታቸውን ላልጨረሱ የመኸር ሰብሎችና ለእንስሳት መኖ እድገት በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኢንስቲትዩቱ አሳውቋል።
በሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች፣ በመካከለኛው፣ ደቡብ ደጋማ አካባቢዎች የሌሊትና የማለዳ ቅዝቃዜ አየር ሁኔታ እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።
በዚህም ቅዝቃዜና ውርጭ ክስተት እድገታቸውን ላልጨረሱ የመስኖ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
የፀሐያማና ደረቃማው ክስተት ደግሞ ለመኸር ሰብል ስብሰባ ሥራ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብሏል ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው።