የትምህርት ቤት ምገባ መርሓ-ግብር በመጠነ ማቋረጥ ላይ የመቀነስ በተማሪዎች የመማር ብቃት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ቤት ምገባ መርሓ-ግብር በመጠነ ማቋረጥ ላይ የመቀነስ በተማሪዎች የመማር ብቃት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተገለጸ

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 የትምህርት ቤት ምገባ መርሓ-ግብር በመጠነ ማቋረጥ ላይ የመቀነስ በተማሪዎች የመማር ብቃት እንዲሁም የተማሪዎች የትምህርት ትኩረት የሚያሳድግ መሆኑ በተግባር እየታየ መሆኑ ተገለጸ።
የትምህርት ቤት ምገባ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።
በአዳማ ከተማ ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ መርሓ-ግብር እየተጠቀሙ ነው ሲል የከተማዋ ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አበራ ቶሌራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተማሪዎች ምገባ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በከተማዋ በሚገኙ ከ60 በላይ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
በከተማዋ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከሚማሩት ውስጥ 60 በመቶው የሚሆኑት በምገባው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ የተቀሩት ተማሪዎች በምገባ ቁሳቁስና በሀብት እጥረት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ከመስተዳደሩና ከክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ተቋም ጋር በመተባበር የተማሪዎች ምገባውን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በከተማው የ'አብዲ ቦሩ' ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ታደሰ አደሬ በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት፤ በትምህርት ቤታቸው 526 ተማሪዎች የምገባ መርሓ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
የተማሪዎች ምገባ መርሐ-ግብር መጀመሩ ለወላጆችም ሆነ ለተማሪዎች ብዙ ጥቅም ያስገኘ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መምህሩ፤ ከምገባው ወዲህ እስከ አሁን ትምህርት ያቋረጠ ተማሪ የለም ብለዋል።
በዚህም መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ የተሻለ መርሐ-ግብር መሆኑንና ለመማር ማስተማር ስራም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

የዚሁ ትምህርት ቤት መምህር ተናኜ ገመዳ ምገባ ከመጀመሩ በፊት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው በተደጋጋሚ እንደሚቀሩ አስታውሰው፤ ክፍል ውስጥም ትምህርታቸውን በአግባቡ አይከታተሉም ነበር ብለዋል።
ምገባ ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ መሆኑን መታዘባቸውን ተናግረዋል።
በአዳማ ከተማ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።