አፍሪካውያን ለኢንደስትሪ ልማትና የእርስበርስ ንግድ መጠናከር ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ለኢንደስትሪ ልማትና የእርስበርስ ንግድ መጠናከር ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 /2015 አፍሪካውያን ለኢንደስትሪ ልማትና የእርስበርስ ንግድ መጠናከር ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኒጀር ርዕሰ መዲና ኒያሚ በተጀመረው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ አገሮች በመካከላቸው ያለው ንግድ እንዲስፋፋና የኢንዱስትሪ ልማቱ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው ለዚህም የአመራሩ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የግል ባለሀብቶች የሚገጥማቸውን መዋቅራዊ መሰናክሎች ለማስወገድና ለማበረታታት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ዕቅድ ተግባራዊ ማድረጓን አቶ ደመቀ አስረድተዋል ።
ኢትዮጵያ የተሟላ አቅም ያላቸውና የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡ 22 የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታ ማካሄዷንና የትምህርት ስርዓቱ ለኢንደስትሪ ልማቱ ብቃት ያለው የሰው ኃይል መፍጠር በሚያስችል ሁኔታ መቀረፁንም ገልፀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ልዩ ስብሰባ ''የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማት ለአካታችና ዘላቂ የኢንዲስትሪ ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ማስፋት'' በሚል ርዕስ ኒጀር መዲና ኒያሚ እየተካሄደ መሆኑንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያን ልዑክ እየመሩ መሆኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት አስታውቋል።