ቀጥታ፡

የጤና አደጋዎችን ለመከላከል ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል - ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 በሕብረተሰቡ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና አደጋዎችን ለመከላከል  ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ድንገተኛ አደጋዎችን መከላከል፣ መመርመርና ምላሽ መስጠት እንዲሁም አገራዊ አቅምን ማጠናከር ዓላማ ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ጦርነት፣ የዝናብ እጥረት፣ መፈናቀልና ሌሎችም በጤና ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸው ይታወቃል።

እነዚህ ፈጣን ቅኝትና ምላሽ አገልግሎትን የሚፈልጉ በሽታዎችን ለመከላከል  ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ይገለጻል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የጤና አደጋዎችን ለመከላከል ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ያጋጠሙ የጤና አደጋዎች ትምህርት የተወሰደባቸው እንዲሁም የጤናው ዘርፍ ያለበትን ደረጃ በመገምገም የተዘጋጀው ስትራቴጂክ እቅድ ለቀጣይ በተሻለ እንዲዘጋጅ ያስቻሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሕብረተሰቡ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና አደጋዎችን ለመከላከል 14 ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡

የውይይት መድረኩም የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል እና ጠቃሚ ግብዓቶችን ለመቅሰም ያግዛል ብለዋል፡፡

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ፤ መድረኩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል ለቅድመ ዝግጅትና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ አቅሞችን መገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።  

የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የመተላለፍ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ገልጸው ይህን ለመከላከል ቅንጅታዊ ሥራ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

መድረኩ በሕብረተሰቡ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረግ ዝግጁነትን ለማሻሻል፣ አቅም ለመገንባት እና የቅኝት ሥራዎችን ለማገዝ ያስችላል ብለዋል፡፡

የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከል የሰው ኃይል፣ የቁሳቁስና የላቦራቶሪ አቅሞችን ለማጠናከርም ይረዳል ብለዋል፡፡

መድረኩን የጤና ሚኒስቴር፣ በአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠሪያ ቢሮ፣ በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ቢሮና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም