ቀጥታ፡

ቋሚ ኮሚቴው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሮጌ ህንጻዎች አፋጣኝ ጥገና እንዲደረግላቸው አሳሰበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመፈራረስ ላይ ያሉ ህንጻዎች አፋጣኝ ጥገና ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመላክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርሲቲው እያደረገ በሚገኘው የመስክ ምልከታ የአገልግሎት መስጫ ህንጻዎች ያሉበትን አቋም ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደጠቆሙት፤ በተለይ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚና በሼህ መሀመድ አል-አሙዲን የተገነባው ላይበረሪ አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ደረጃ እየፈራረሱ በመሆኑ አፋጣኝ ጥገና ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው አቅምም ሆነ በሌሎች አካላት ለተጎዱ ህንጻዎች አፋጣኝ መፍትሄ ይሰጥ ዘንድ ቋሚ ኮሚቴው ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከጉብኝታቸው በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ኮሌጆች ከተውጣጡ የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች ጋር መወያየታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም