ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 10 ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው አቅም መተዳደር ይጀምራሉ- ትምህርት ሚኒስቴር

ሐዋሳ፣ ህዳር 14/2015 (ኢዜአ) በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ትውልድ የሆኑ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንደሚጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሰረታዊ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን አብርሃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እየተደረጉ ያሉ የለውጥ ስራዎች  የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ የተቀመጠውን ፍኖተ ካርታ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ማድረግ ከሪፎርም ስራዎቹ ተጠቃሽ ሲሆኑ የአሰራር ስርዓቶች፣ የህግ ማዕቀፎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራሱን ችሎ እንደሚተዳደርና በዚህም የሚሰጠውን ተልእኮ በአግባቡ መፈጸም የሚያስችል አቅም በመፍጠር ጥራት ያለው የትምህርትና የምርምር ስራ ያከናውናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ አሁን ካለው አቅምና የትምህርት ፕሮግራሞች አንጻር ራስ ገዝ ለማድረግ ቀዳሚ ሆኖ መመረጡን ተናግረዋል፡፡

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የምርምር ተልእኮ በተሰጣቸውና የመጀመሪያው ትውልድ ተብለው የተለዩ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን በራሳቸው ወደ ማስተዳደር ይገባሉ ብለዋል፡፡

እንደ ሃዋሳ፣ ጅማ፣ ባህርዳር፣  ጎንደር፣ ጂማ፣ መቀሌና አንድ  ሳይንስና ቴክኖሎጂ  ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የምርምር ተልእኮ የተሰጣቸው ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ የማድረጉ ስራ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተወሰደ ልምድ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ ራስ ገዝ ሲሆኑ ሙሉ በሙሉ በመንግስት አይተዳደሩም ማለት አለመሆኑን የገለጹት ዶክተር ሰለሞን ከተጠያቂነትና ከሃላፊነት ጋር ተልእኮዋቸውን የሚፈጽሙበት አሰራር መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ራስ  ገዝ መሆኑ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ  ጉዳዮች  ለመፍታት የሚያስችለውን ተልእኮ በተገቢው እንዲወጣ ያስችላል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎችም ራስ ገዝ ሆነው እንዲወጡ ማድረግ አቅማቸውን አጠናክረው የተሻለ ስራ ለመስራት የሚችሉበት ዕድል እንደሚፈጠርና የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ራስ ገዝ መሆኑ  የምርምርና  ማህበረሰብ  አገልግሎቱን  ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እንዲያሰርጽ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ራሱን ችሎ ሲወጣ የሚጠቀማቸው የፋይናንስ፣ የሰው ሃይል ቅጥር፣ የንብረት አስተዳደርና የሰራተኛ አያያዝ ህጎችም አስቀድመው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የገቢ አቅሙን በሁሉትና ሶስት እጥፍ በማሳደግ አገልግሎቱን ማጠናከር እንደሚችልም ፕሮፌሰር ጣሰው ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም