የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ500 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ስምምነት አካሄደ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 14/2015 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ፓሮን ትሬዲንግ ከተሰኘው ሀገር በቀል ድርጅት ጋር የ500 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ስምምነት አካሄደ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንና ፓሮን ትሬዲንግ የተባለው ሀገር በቀል ኩባንያ በባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብቶ ምርት ለማምረት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ እና የፓሮን ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ አስሬ ተፈራርመዋል።

ድርጅቱ በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማራ አገር በቀል ኩባንያ ሲሆን በፓርኩ 500 ሚሊዮን ብር ሀብት ፈሰስ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

በስምምነቱ መሰረት ድርጅቱ ሁለት ሄክታር የለማ መሬት የተረከበ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በመላው አገሪቱ በገነባቸው 13 ኢንዱስትሪዎች የውጭ እና አገር በቀል ባለሀብቶችን በማስገባት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እያበረከተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም