ቀጥታ፡

የጉጂ ዞን ሕዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ነገሌ ኢዜአ ህዳር 14.2015 ዓ.ም --የጉጂ ዞን ሕዝብ በሰባት ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድና በስጦታ መልክ ድጋፍ አደረገ፡፡

በዞኑ ለአራተኛ ጊዜ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን በዞኑ የግድቡ ግንባታ ሀብት አሰባሳቢ ምክር ቤት ገልጿል፡፡

የምክር ቤቱ ጸሀፊና የዞኑ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዮሀንስ ኦልኮ ባለፉት ሰባት ወራት ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድና በስጦታ መልክ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ከሚያዝያ 2014 እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም 27 ሚሊዮን ብር ከቦንድ ሽያጭና በስጦታ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 24 ሚሊዮን ብር ከቦንድ ሽያጭ የተገኘ ሲሆን 3 ሚሊዮኑ ደግሞ በስጦታ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ድጋፉ የተደረገው ከዞኑ ነገሌ፣ አዶላና ሻኪሶ ከተሞችን ጨምሮ በ18 ወረዳዎች የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ በሶስት ዙር ለግድቡ ግንባታ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድና በስጦታ እንዲሁም በአይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም