የወባ በሽታን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ተግባር እያከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ዞኖች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የወባ በሽታን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ተግባር እያከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ዞኖች ገለጹ
መቱ፣ አምቦ፣ ሻሸመኔ (ኢዜአ) ህዳር 14 ቀን 2015 በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች የወባ በሽታን ቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን ገለጹ።
ኢዜአ የወባ በሽታን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ የኢሉባቦር፣ የምዕራብ ሸዋና ምዕራብ አርሲ ዞን የጤና ጽህፈት ቤቶችን አነጋግሯል።
የወባ በሽታን ለመከላከል ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት የኢሉባቦር ዞን ጤና ጽሕፈት ቤት የወባ በሽታ መከላከል ዘርፍ አስተባባሪ አቶ በላይ አስፋው ናቸው።
በዞኑ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል ግንዛቤ የሚያሳድጉ ትምህርቶች በየቦታው እየተሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ውሃ ያቆሩ አከባቢዎችን የማፋሰስ፣ ቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት ማድረግ፣ የአልጋ አጎበር ለነዋሪዎች የማደል ስራዎች በስፋት እየተሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአልጋ አጎበር እጥረት እንዳያጋጥም ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በተሰራው ስራ ቅድሚያ ሊያገኙ ለሚገባቸው ወረዳዎች ከ100 ሺህ በላይ አጎበሮችን የማደል ስራ መከናወኑንም አንስተዋል።
ከመድኃኒት አቅርቦት አንጻርም የተሻለ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው የመከላከል ስራው የሁሉንም ተሳትፎና ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም እየተሳተፈበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም የአጎበር እደላና የአጠቃቀም እንዲሁም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ የማያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ አርሲ ዞን የወባ በሽታን ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተስራ መሆኑን የዞኑ ጤና ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
በዞኑ የወባ በሽታ ለመከላከል አስፈላጊ የመከላከያ ዘዴዎች እንዲተገበሩ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ግርማ ያዛቸው ተናግረዋል።
በዞኑ ባለፈው ክረምት ከ24 ሺህ በላይ ስዎች በበሽታው መጠቃታቸውን አስታውሰው በቅርቡ በተወሰደ ናሙና በሽታው በ8 ሺህ ሰዎች ላይ መገኘቱን ጠቁመዋል።
በሽታው በዞኑ ሙቀታማ አየር ንብርት ያላችው ወንዶ፣ ሲራሮ እና ሄባን አርሲ ወረዳዎች ላይ በስፋት መታየቱን ተናግረዋል።
በወረዳዎቹ ለህብረተስቡ ግንዛቤ እየተሰጠ መሆኑንና የቤት ለቤት የፀረ ወባ በሽታ ከሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ የወባ በሽታ የታየባቸው ወረዳዎች 370 ሺህ 950 በላይ አጎበር መሰራጭቱን አስገንዝበዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት የወባ ማጥፋትና መከላከል ባለሞያ አቶ አባተ አርጋው በበኩላቸው የወባ በሽታ በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሕብረተሰቡ በአካባቢ ጽዳት፣ በአልጋ አጎበር አጠቃቀም ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ መደረጉን ጠቁመው ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆነ ረግረጋማና ውሃ ያቆሩ ቦታዎች የማድረቅና የማፋሰስ ሥራ በየጊዜው ሲከናወን መቆቱንም ተናግረዋል።
እስካሁን በዞኑ የወባ በሽታ ሊከሰት እንደሚችል አመላካች ነገር ባለመኖሩ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ አለመሆኑንም አስረድተዋል።
በቅድመ መከላከል ሥራው ከተሳተፉ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አበራሽ ገመቹ፤ በአካባቢያቸው የወባ በሽታ ቅድመ መከላከል ሥራ በመሰራቱ ከበሽታው ስጋት ነጻ መሆናችውን ገልጸዋል።
ለወባ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን ከማጽዳት ጎን ለጎን የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከበሽታው መከላከል እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ በዬቲ ጉርሜሳ ናቸው።
በአካባቢያቸው በተመደቡ የጤና ባለሙያዎች ምክር የመኖሪያ ሰፈራቸውን በሚገባ በማጽዳትና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን ከወባ ወረርሽኝ ስጋት ነጻ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ኩታዬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፍጹም በየነ ናቸው፡፡