ሜክሲኮ በቱሪዝም ልማት ያላትን የላቀ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማጋራትና በዘርፉ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት አላት- አምባሳደር ቪክቶር ትሬቪኖ

24

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 13/2015 ሜክሲኮ በቱሪዝም ልማት ያላትን የላቀ ልምድና ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማጋራትና በዘርፉ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ያላት መሆኑን በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ቪክቶር ትሬቪኖ ገለጹ።

አምባሳደሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሜክሲኮ በቱሪዝም ልማት ያስመዘገበችውን ስኬትና ተሞክሮ በማጋራት በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ እንደምትሰራ ተናግረዋል።

ሜክሲኮ በቱሪዝም ዘርፍ ከዓለም አሥር ቀዳሚ አገራት መካከል መሆኗን ጠቅሰው፤ እንደ ኢትዮጵያ በጥሩ ሂደት ላይ ላሉ አገሮች ተሞክሮዋ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአውሮፓ የቱሪዝም እና ንግድ ምክር ቤትም ከሰባት ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ2015 ኢትዮጵያን ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ አገር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል።

በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዘርፉን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ቱሪዝም የልማትና ብልፅግና መሰረት" ከሆኑ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያና ሜክሲኮ ያላቸውን ጥንታዊና ታሪካዊ የቱሪዝም ሥፍራ በማልማት ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ እንዲሆኑ በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አምባሳደር ቪክቶር ትሬቪኖ አንስተዋል።  

ኢትዮጵያና ሜክሲኮ በቱሪዝም ዘርፍ የሚያመሳስላቸው በርካታ ነገር መኖሩን ጠቅሰው፤ በትብብር መሥራታቸው ሁለቱንም አገሮች ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ያሉ አኩሪ መዳረሻ ሥፍራዎች እንዳላቸው ሁሉ፤ በሜክሲኮም ፒራሚዶችን ጨምሮ ሌሎች የመዳረሻ ሥፍራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሜክሲኮ በመልክዐ-ምድራዊ አቀማመጥ የተራራቁ ቢሆንም "ኢትዮጵያ በልባችን ስላለች በሜክሲኮ የኢትዮጵያ አደባባይ አለን" ብለዋል።

በተመሳሳይም በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሜክሲኮ አደባባይ መኖሩ ሁለቱን አገራት ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት የሚያሳይ እንደሆነ አንስተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) 13 የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ የኢትዮጵያ ቅርሶች እውቅና በመስጠት የዓለም ሕዝቦች ወካይ ቅርስ እንዲሆኑ አድርጓል።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት የበለፀገ ብዝኃ-ሕይወት እና ጥብቅ ሥፍራን በመያዝ ከሰሜን እስከ ባሌ ተራሮች፣ ከደንከል በረሃ እስከ ሌሎች ዝቅተኛ ሥፍራዎች ድረስ አስደናቂ የመሬት ገጽታን በመያዝ ኢትዮጵያ አስደናቂ የቱሪዝም ሃብት ያላት አገር መሆኗ ይታወቃል።

ኢትዮጵያም ካሏት ታሪካዊ፣ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶች በተጨማሪ በአርኪዮሎጂ እና በፓሊዮሎጂ የቅሪተ-አካል የምርምር ሥራ “የሰው ልጅ መገኛ” ተብላ የተሰየመች በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራ ያላት አገር ነች።

በአፋር በረሃማ ቦታ በተካሄደው የአርኪዮሎጂ ምርምር ሚሊዮን ዓመታትን ያስቆጠረና የመጀመሪያው የሰው ልጅ ቅሪተ-አካል "ሉሲ" መገኘቱ ይታወቃል።

የኢትዮ-ሜክሲኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ. በ1936 የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም