በመስዋዕትነት የተገኘውን ስኬት ከዳር ለማድረስ ከህወሓት ጎን እንደሚቆሙ እህት ድርጅቶች አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
በመስዋዕትነት የተገኘውን ስኬት ከዳር ለማድረስ ከህወሓት ጎን እንደሚቆሙ እህት ድርጅቶች አረጋገጡ
መቀሌ መስከረም 16/2011 ህወሓት ለህዝቦች መብት መከበር ሲል ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር በከፈለው መስዋዕትነት የተገኘውን ስኬት ከዳር ለማድረስ ከጎኑ እንደሚቆሙ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አረጋገጡ። በህወሓት 13ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እህት ድርጅቶች ባስተላለፉት የድጋፍ መልዕክት እንዳስታወቁት፣ ህወሓት በትግል ወቅት የትግራይ ክልል ህዝብን አስተባብሮ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሏል። ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋራ በመሆን ባደረገው ትግል የተገኘው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ቱርፋት ከክልሉ ህዝብ አልፎ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረጉን ድርጅቶቹ ተናግረዋል። የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ተወካይ የድጋፍ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ እንዳሉት፣ ለዘመናት በተካሄደው መራራ ትግል የተገኙ ስኬቶች የክልሉን ህዝብ ብቻ ሳይሆን መላውን የአማራ ክልል ህዝብንም ተጠቃሚ አድርጓል። የአማራና የትግራይ ክልል ህዝቦች ከጉርብትና በላይ በተካሄዱ የአንገዛም ባይነት የትግል ሂደቶች በደምና አጥንት የተሳሳሩ ህዝቦች መሆናቸውንም ነው የገለጹት። "ሁለቱም ህዝቦች አንጸባራቂ ታሪክ ያላቸው፣ አብረው በፍቅር የኖሩ፣ የተዋለዱና የተዛመዱ ህዝቦች ናቸው" ያሉት የብአዴን ተወካይ፣ መቼውንም እንደማይነጣጠሉ ተናግረዋል። " የሁለቱም ህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት በደም የተሳሰረ በመሆኑ መልካም ጉርብትናቸውን በትእግስትና በአርቆ አሳቢነት በማጠናከር በጋራ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። የትግራይ ክልል ህዝብና ህወሓት በትግል ሂደታቸው ታሪክና ዘመን የማይሽረው አንጸባራቂ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የገለጹት ተወካዩ፣ በወቅቱ በርካታ ፈተናዎችን ማለፉቸውንም አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በጽናትና በስኬት ለማለፍ ብአዴን ከህወሓት ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል። " ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ የቆየውን ግፍ ለማስወገድ የተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ለስኬት በመብቃቱ መቼም አይዘነጋም " ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ተወካይ ናቸው። እንደተወካዩ ገለጻ ህወሓት በህዝቦች መስዋዕትነት የተገኙ ስኬቶች መና እንዳይቀሩ እንደ እስከዛሬው ሁሉ በሂደት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎችና ተግዳሮቶችን አሁንም በጽናት እያለፈ ይገኛል። "ህወሓት ያለውን የዳበረ የትግል ተሞክሮ በመጠቀም በቀጣይ ተተኪ ወጣቶችና ምሁራንን በማፍራት ትግሉን ማስቀጠል ይጠበቅበታል" ብለዋል። ህወሓት በጉባኤው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ከስኬት እንዲደርሱ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከድርጅቱ ጎን በመቆም ተባብሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዲን) ተወካይ በበኩላቸው ህወሓትና የትግራይ ክልል ህዝብ ጭቆናና በደልን ላለመቀበል ችግሮችን ፊት ለፊት ሲጋፈጡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። ህወሓት የክልሉን ህዝብ በተደራጃ መልኩ በማታገልና እልህ አስጨራሽ ትግል በማካሄድ የአንበሳውን ድርሻ ማበርከቱንም ነው ያስታወሱት። የህዝብን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎችን አንግቦ ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር ባደረገው ትግል ስኬትን ለተጎናጸፈው ህወሓት ደኢህዴን ከፍተኛ አድናቆት እንዳለውም ተወካዩ ተናግረዋል። "በቀጣይም ደኢህዴን ለላቀ ለውጥ ከህወሓት ጋር ይቆማል" ብለዋል። ዛሬ በተጀመረው 13ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የአፋር ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የቤንሻጉል ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የዓረና ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲና ሌሎች የፖሊቲካ ድርጅቶች የድጋፍ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡