የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የአቅመ ደካሞችን የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀመረ

136

አዲስ አበባ/ኢዜአ/ህዳር 13/2015  የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በመዲናዋ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአቅመ ደካማ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀመረ፡፡

በተጨማሪም በክፍለ ከተማው ለሚገኘው ወረዳ 03 ጽሕፈት ቤት 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አስቴር ዳዊት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን የሳይበር ምህዳር ለመጠበቅ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ተቋማት የመረጃ አያያዛቸውን በማዘመን ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እገዛ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በዛሬው እለት የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት ለሚገኝበት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ጽሕፈት ቤት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በ2 ሚሊዮን ብር ወጪ በወረዳው የሚኖሩ የሁለት አቅመ ደካማ ወገኖችን የመኖሪያ ቤት እድሳት አስጀምሯል፡፡

የቤት እድሳቱም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ነው የገለጹት፡፡

የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አስቴር ደሳለኝ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከዚህ ቀደም በወረዳው የሚገኙ አቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት ከማደስ ባሻገር የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

የተደረገላቸው ድጋፍ ለሕብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ገልጸው፤ ለድጋፉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ብሩክ ከድር በበኩላቸው፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የተለያዩ ተቋማት ዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ በመደገፍ ረገድ በአርአያነት የሚነሳ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በክፍለ ከተማውም መሰል የበጎ አድራጎት ሥራ ማከናወኑን ለአብነት አንስተው፤ በዛሬው እለት ያከናወነውን የበጎ አገልግሎት ሥራ አድንቀዋል፡፡

ክፍለ ከተማው የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት ከማደስ ባሻገር ሌሎች ሰው ተኮር ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያነሱት፡፡

ተቋሙ ዛሬ ያስጀመረው የቤት እድሳት ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ አስረበብ መንገሻ፤ የመኖሪያ ቤታቸው ለዘመናት ምንም አይነት እድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ኑሯቸውን ይገፉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የመኖሪያ ቤታቸውን እድሳት በማስጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም