የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የተዋቀረው ኮሚቴ ውጤታማ እንዲሆን የሕዝቡ ጠንካራ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል- ጠበቃና የሕግ አማካሪ

25

አዲስ አበባ/ኢዜአ/ህዳር 13/2015 በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የተዋቀረው ኮሚቴ ውጤታማ እንዲሆን የሕዝቡ ጠንካራ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን አንድ ጠበቃና የሕግ አማካሪ ተናገሩ።

የሙስና ወንጀል በተለይም በመሬት አስተዳደር፣ በሕዝብ አገልግሎት መስጫዎችና ሌሎችም ዘርፎች እየሰፋ መጥቶ የአገር እድገት ማነቆና የሕዝብ ምሬት ዋነኛ ምክንያት እየሆነ መጥቷል።    

የወንጀሉ ሥር እየሰደደ መምጣትና መበራከት ደግሞ የአገርን ሕልውና በመፈታተን ዜጎችን ለችግርና እንግልት እየዳረገ ይገኛል።       

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያም በኢትዮጵያ ሙስና የልማትና እድገት ማነቆ፤ የሕዝብ የምሬት ምክንያት መሆኑ ተባብሶ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ገልፀው፤ በቅርቡም የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ በማዋቀር ይፋ አድርገዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ተዋናይ ሙላቱ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዋቀረው ኮሚቴ በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስናን ለመከላከል እንደ በጎ እርምጃ የሚወሰድ ነው ብለዋል።       

የተቋቋመው ኮሚቴ ውጤታማ እንዲሆን በተለይም የሕዝቡ ትብብርና ተሳትፎ በእጅጉ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በእጅጉ እየበረታ የመጣው የሙስና ወንጀል ጉዳይ በፍጥነት መፍትሔ የሚያስፈልገው በመሆኑ  መንግሥት  ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አድንቀዋል።

የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የተዋቀረው ኮሚቴም ከዚህ በፊት ከነበረው አካሄድ በተሻለ መልኩ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የሕዝቡ የአመለካከት ለውጥ እንዲሁም በመከላከል ሂደቱ ጠንካራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የፀረ-ሙስና ኮሚሽንን አቅም መገንባትም ሌላው ትኩረት የሚሻና ውጤታማ ከሚያደርጉ አካሄዶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አመላክተዋል።

ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን መፈተሽና ክፍተቶችን መዝጋትም ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል መፍትሔ መሆኑን ነው ያብራሩት።

የሙስና ወንጀልን በተመለከተ የሕግ ክፍተት ባይኖርም አፈጻጸም ላይ የሚጠበቀውን ያህል እየተሰራበት አይደለም ያሉት ባለሙያው ለመከላከል የጋራ ጥረትና ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል።

በሙስና ተሳትፎ ያደረጉ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድም ጥፋቱ በሌሎች እንዳይደገም የሚያደርግ በመሆኑ የበለጠ ሊሰራበት እንደሚገባም ነው አጽንኦት የሰጡት።    

በአንድ በኩል የመንግሥት ሕጎች፣ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት የማጥፋት ሥራ በመስራት በሌላ በኩል ደግሞ የሙስና ተዋንያንን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅ ተግባር የሚከናወን መሆኑን መንግስት መግለጹ ይታወሳል።

መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም