ቢሮው የአዲስ አበባ ከተማን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከ10 በላይ ከሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

134

ሕዳር 13/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ የማህበረሰብ አደረጃጀቶችን ጨምሮ ከ10 በላይ ከሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ስምምነት የተፈራረመው በቅርቡ በተዘጋጀው እና ስራ ላይ በዋለው የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት ደንብ ቁጥር 140/2014 ዙሪያ በትብብር ለመስራት ነው፡፡

አዲስ የወጣው የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት ደንብ ከወረዳ በታች ያሉ የመንደር፣ የብሎክና የቀጠና የሰላም ሰራዊት አደረጃጀቶችን ስልጣንና ኃላፊነትን የሚወስን ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ መላኩ ታምሩ የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ማስጠበቅ የሚቻለው ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የስምምነት ፊርማው የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት በማስከበር ረገድ ኀብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ስምምነቱ በሰላም ሰራዊት አደረጃጀት የሚሳተፉ አካላት ኃላፊነታቸውን አውቀው ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እንደሚያግዝም  ነው የገለጹት፡፡

የሰላም ስምምነቱ በከተማ ደረጃ የተዋቀረው የሰላም ምክር ቤት ስራን እንደሚያግዝ የተናገሩት ደግሞ  የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ናቸው፡፡

ስምምነቱ ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው እንዲሰሩ ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ ከ143 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሰላም ሰራዊት አባላት መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸውና በሚኖሩበት አካባቢ ተደራጅተው የሰላምና የጸጥታ ስራውን እያገዙ መሆኑም ነው በስምምነት ፊርማ ስነ-ስርዓቱ የተገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም