የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው-የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

15

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 13/2015 በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በአማራጭ የታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክፊኬሽን ፕሮግራም እና የኤሌክትሪክና ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም ከተጀመረበት 1998 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ8 ሺህ በላይ ከተሞችንና የገጠር ቀበሌዎችን በኤሌክትሪክ ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል።

ፕሮግራሙ በተጀመረበት 1998 ዓ.ም 690 ከተሞች ብቻ ተጠቃሚ የነበሩ መሆኑና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት የነበረው ህዝብ ቁጥር ከ10 በመቶ በታች እንደነበር ተጠቅሷል።

መንግስት በሂደት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማሳደግ በወሰዳቸው እርምጃዎች ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸው ነው በውይይቱ የተገለጸው።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ፤ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበሩት የኤሌክትሪክፊኬሽንና የብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክቶች ውጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።

በዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት በየዓመቱ እያደገ ቢሆንም፤ አሁንም በኢትዮጵያ አገልግሎቱን ያላገኘውን 60 በመቶ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ በአማራጭ የታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለፁት።

ለስኬቱም የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ ባሉ እምቅ የኃይል ምንጮች ሙዓለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት በማሳደግ ረገድ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰሩ ተግባራት የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትንና የተጠቃሚዎችን ቁጥር አሁን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

መንግስት በ10 ዓመት መሪ የልማት እቅዱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ ዜጎች ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግብ መያዙን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም