ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ለዘመናት የዘለቀውን የሽምግልና እሴት ጠብቆ መቀጠል ይገባል- የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ - ኢዜአ አማርኛ
ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ለዘመናት የዘለቀውን የሽምግልና እሴት ጠብቆ መቀጠል ይገባል- የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ
ሕዳር 13/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ለዘመናት የዘለቀውን የሽምግልና እሴት ጠብቆ መቀጠል እንደሚገባ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባላት አመለከቱ።
በኢትዮጵያዊያን ባህል ሽምግልና መንፈሣዊ መሠረት ያለው ለዕርቅ፣ ለፍቅርና ለሠላም የቆመ፤ ጥልን በዕርቅና ይቅርታ የሰዎች ሰላማዊ ነባራዊ ሁኔታ ማስተሳሰሪያ እሴት መሆኑ ይታወቃል።
የሽምግልና ሥርዓት እንደ የአካባቢው ስም እና ክዋኔው ቢለያይም በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ስነ-ምግባራዊ እና መንፈሳዊ መልክ ይዞ በሚዛናዊነት ለዘመናት የዘለቀ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት ነው።
የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባል መላከ ጥበብ ስሜነህ አበበ፤ ሽምግልና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ከበሬታ እና ኃያልነት በባህሎች እና በኃይማኖታዊ አስተምህሮ ያሰናስሉታል።
የሽምግልና እሴት የካበተ ዕውቀት ያለበት፣ ጥላቻና ቂምን የሚሽር፣ ቁጣን የሚያበርድ፣ በይቅርታ እርቅን በማጽናት ሰላም የሚሰፍንበት ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
በመሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ለዘመናት የዘለቀውን የሽምግልና እሴት ጠብቆ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
የመማክርት ጉባዔው አባል ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር፤ በኢትዮጵያ ጥላቻንና መቃቃርን በውይይትና በሽምግልና በመፍታት ሰላማዊና የተረጋጋች አገር መገንባት ይገባል ይላሉ።
ከአሁን ቀደም የሽማግሌዎች "ምክር አይበጅም ባይነት" ባለመሰማቱ በርካታ ችግሮች መድረሳቸውን አስታውሰው፤ ከደረሱ ጥፋቶች በመማር ቀጣይ ለዕርቅ፣ ይቅርታና ሠላም ትልቅ ሥፍራ መስጠት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ ሰብሳቢ ዶክተር ተስፋጺዮን ደለለው እና የመማክርት ጉባዔው አባል አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፤ የሽምግልና ሥርዓታችን የችግሮች መፍቻ ቁልፍና የአብሮነት ማጠናከሪያ የጋራ እሴት መሆኑን ይናገራሉ።
በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በሽምግልና መፍታት የሚቻልበት የካበተ ልምድ መኖሩን ጠቅሰው፤ ሽማግሌዎች ተደማጭ፤ ተሸምጋዮች ደግሞ አድማጭ እየሆኑ ችግሮቻችንን በጋራና በትብብር መፍታት አለብን ብለዋል።
የሰሜኑን ግጭት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሠላም ስምምነት ለኢትዮጵያ ትልቅ እፎይታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሠላም ስምምነቱ ውጤታማነት የሁሉም ቀና ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።