የኢትዮጵያ ጀግኖችን ታሪክ ለትውልዱ በማስተማር ሀገር ወዳድ ዜጋን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጀግኖችን ታሪክ ለትውልዱ በማስተማር ሀገር ወዳድ ዜጋን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሕዳር 13/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጀግኖችን ታሪክ ለትውልዱ በማስተማር ሀገር ወዳድ ዜጋን የማፍራት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በመዲናዋ ልደታ ክፍለ ከተማ በአዲስ መልኩ የተገነባው የሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ትምህርት ቤት እና ሐውልት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአብዲሳ አጋ ቤተሰቦች፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላትና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተመርቋል።

በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች እንዳሉት ታሪክ ሰርተው ያለፉ ጀግኖቻችንን በመዘከር እና በማስተማር ትውልድ እንዲገነባበት መስራት ያስፈልጋል።
ለዚህም ለሀገር ትልቅ ውለታ ያበረከቱ ጀግኖችን ታሪክ በስርዓተ ትምህርት በማካተት በየትምህርት ቤቶችና ሌሎችም የማስተማሪያ ዘዴዎች ለትውልዱ የማስተማር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።
በዚህም የጀግኖችን አርዓያ በመከተል ለኢትዮጵያ ዕድገት የሚተጋ ሀገር ወዳድ ዜጋን የማፍራት ስራን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የከተማ አስተዳደሩም በሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ስም በ1965 ዓም ተገንብቶ የነበረውን በእርጅና የፈራረሰውን ትምህርት ቤት በአዲስ መልኩ እንዲገነባ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ አብዲሳ አጋን የሚዘክር ሀውልት በማቆም ለትውልዱ የጀግኖችን ታሪክ ለማውረስ መስራቱን ጠቁመዋል።
አብዲሳ አጋ በዓለም የታወቀበት የጀግንነት ታሪክ ትውልድን በሀገር ፍቅር ለመገንባት የምንጠቀምበት በመሆኑ እንኮራለን ነው ያሉት።
የሌተናል ኮሎኔል አብዲሳን ታሪክ ስናወሳ ጽናትና ጀግንነትን ለአገር ትልቅ ስራ ሰርቶ ማለፍን ያስተምረናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው፤ ድንበርና እስር ካልገደበው የአብዲሳ አጋ የጀግንነት ታሪክ ተማሪዎች ብዙ እንደሚማሩ ተናግረዋል።
የጀግኖች ታሪክ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካትቶ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ትውልዱ እንዲማርበት የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካይ ሻምበል ተድላ ጸጥአርጋቸው በበኩላቸው ከአብዲሳ አጋ ታሪክ ትውልድ እንዲማርበት ከተማ አስተዳደሩ የሰራው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ሌተናል ኮሎኔል አብዲሳ ከአገር አልፎ በአውሮፓ ምድር የዘለቀና በጠላት ጭምር የተመሰከረለት ጀግና መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ በጣሊያን እስረኞችን ከእስር በማስለቀቅ እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በጣሊያን ሮም ያውለበለበ የኢትዮጵያ ጀግና መሆኑን ለትውልድ ማስተማር ይገባል ነው ያሉት።
የሌተናል ኮለኔል አብዲሳ አጋ ልጅ ወይዘሮ አኒሳ አብዲሳ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ጀግናው በትውልድ ልብ ውስጥ ህያው ሆኖ ታሪኩ እንዲዘከር መታሰቢያ በመቆሙ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌተናል ኮለኔል አብዲሳ አጋ በወላጋ ነጆ በ1911 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን በ14 ዓመታቸው የክብር ዘበኛን በመቀላቀል ከዚያም ከገነት ጦር ትምህርት ቤት በ50 አለቃ ማዕረግ ተመርቀዋል።
ፋሽስት ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ከሌሎች አርበኞች ጋር ሀገሩን ከጠላት ተከላክለዋል፣በተለያዩ ጦር ሜዳዎች ጀብዱ በመስራት በ1970 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።