በደቡብ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐግብር የወተት፣ የማርና የስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው

19

ሀላባ ቁሊቶ፣ (ኢዜአ) ህዳር 13/ 2015 በደቡብ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሐግብር የወተት፣ የዶሮ፣ የማርና የስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

ክልላዊ የሌማት ትሩፋት የንቅናቄ መድረክ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ኡስማን ሱሩር እንዳሉት፤ በሌማት ትሩፋት የወተት፣ የዶሮ፣ የማርና የስጋ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ ከእንስሳት ሃብት ልማት፣ ከስራስር ሰብሎች እና ከእንሰት ተክል ጋር ተሳስሮ እንደሚተገበር የጠቆሙት ሃላፊው፤ የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩን ስኬታማ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ስራ እስከ 35 ሊትር ወተት የሚሰጡ ላሞች ማግኘት እንደተቻለም ጠቁመዋል።

በክልሉ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን የወተት ላሞች እንደሚገኙና ከዚህ ውስጥ 93 በመቶ የሚሆኑት የሀገረሰብ ላሞች መሆናቸውን ገልጸው፤ የወተት ምርት ከነበረበት ሁለት ሊትር በአማካይ 14 ሊትር ለማድረስ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የዶሮ ዝርያንም በማሻሻል ከአንድ ዶሮ በአመት እየተገኘ ያለውን 50 እንቁላል ወደ 280 ለማሳደግ እንሰራለን ብለዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልሉ  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም