ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰጠው ልዩ ትኩረት በውጭ ገበያ የምርት ጥራትና አቅርቦት ላይ ውጤት አምጥቷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 13/ 2015 ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰጠው ልዩ ትኩረት በውጭ ገበያ የምርት ጥራትና አቅርቦት ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር አስታወቀ።

በኮቪድ ወረርሽኝና ሌሎች ምክንያቶች የዓለም የወጭ ንግድ እንቅስቃሴ የተዳከመበት አጋጣሚ በመፈጠሩ አገሮች በብዙ ችግር ውስጥ ማለፋቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያም የዚሁ ተጽእኖ ገፈት ቀማሽ በመሆኗ በተለይም ጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ለውጪ ገበያ በሚያቀርቡ ላኪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ይነሳል።

በመሆኑም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሰጠችው ልዩ ትኩረት በተለይም በውጭ ገበያ የምርት ጥራትና አቅርቦት ላይ የሚታይ ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር አስታውቋል።

የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ አስማረ፤ እንደሚሉት የዘርፉ ዳግም መነቃቃት ለላኪዎችም ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል።

ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምረው የሚልኩ ኢንዱስትሪዎችም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል።

ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ማህበሩ 230 ሺህ ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ ወደ ውጪ ለመላክ እየተዘጋጀ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

ከምርት ሒደቱ ጀምሮ ለውጭ ገበያ እስኪቀርብ ድረስ ለሚሳተፉ አካላት ስለምርት አያያዝ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለአርሶ አደሮችም ከማሳ ጀምሮ አጠቃላይ የምርት ሂደት ማህበሩ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዱባይ ዓለም አቀፍ የቅባት እህሎች ኮንፌዴሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሬንዲ ዳኩሬት፤ ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠችው ልዩ ትኩረት ጥራት ያላቸው ምርቶች ለዓለም ገበያ በመቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚገኝባቸው የግብርና ምርቶች መካከል መሆናቸውንም ጠቅስዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም