ቀጥታ፡

የአዳማ የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የአካባቢውን የሃይል አቅርቦት አሻሽሎታል---የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል

ህዳር 13 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአዳማ የተገነባው የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለኢንዲስትሪ ፓርኮች የተሻለ አገልግሎት እንዲቀርብ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።

ተቋሙ ጣቢያውን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች አስጎብኝቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የትራንስሚሽንና ሰብስቴሽን ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስፈጻሚ ክብሮም ካህሳይ ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት ጣቢያው 250 ሜጋ ዋት ሃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነው።

ጣቢያው በዋናነት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች በተሻለ ሁኔታ ሃይል እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ስራ አስፈጻሚው እንደሚሉት ለፕሮጀክቱ ግንባታ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ተጨማሪ 150 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ወጪውን ሙሉ በሙሉ የሸፈነው መንግስት ነው።

ከወራት በፊት ስራ የጀመረው ጣቢያው በአሁኑ ወቅት በተሻለ ሁኔታ የኤሌክትሪክ ሃይል እየሰጠ መሆኑን አመልክተው የአዳማንና አካባቢውን ሃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም