የፓኪስታን ባለሀብቶች መዋለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያውሉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የፓኪስታን ባለሀብቶች መዋለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያውሉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 13/2015 የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያውሉ በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ጥሪ አቀረቡ።
አምባሳደሩ ከፓኪስታኑ ጂኤስ ባንክ መስራች ጃሃንጋሪ ሲዲቁ ጋር ባደረጉት ውይይት የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ምቹ አማራጮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከጥቂት ወራት በፊት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን ያስታወሱት አምባሳደሩ የካፒታል ኢኮኖሚን ለመተግበር ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተለይ በግብርናው፣አግሮ ፕሮሰሲንግ፣በማኑፋክቸሪንግ፣ማዕድን፣ጨርቃጨርቅ፣ጤና፣ቱሪዝም እንዲሁም በአይሲቲ ዘርፎች የውጭ ባለሀብቶች ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉባቸው ሰፊ አማራጮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
መንግስት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ እየሰራ ነው ያሉት አምባሳደሩ ከ96 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል ከውሃ እና ከንፋስ ሃይል እንደሚመረት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የንጹህ ሃይል አቅርቦትን ለኬኒያ፣ሱዳን እንዲሁም ጁቡቲ ኤክስፖርት እንደምታደርግ ገልጸው ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ቀጠናዊ ትስስርን ለማስፋት እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ ካለችበት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ለፓኪስታን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆን እንደምትችልም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ፓኪስታኗ ካራቺ ከተማ በረራ እንዲሚጀምር አስታውቀው ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ትስስር ለማጎልበትና ሀገራቱን ለማስተሳሰር የጎላ አስተዋጾ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
የጂኤስ ባንክ መስራች ጃሀንጋሪ ሲዲቁ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ባለው የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ባለሀብቱ በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመመልከት የልኡክ ቡድናቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡም አስታውቀዋል።
በተያያዘም አምባሳደሩ በፓኪስታን ከሚገኘው አሪፍ ሀቢብ ሀላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን እቃዎች እንዲሁም የማዳበሪያ ምርት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ አብራርተዋል።
በአሁኑ ግዜ በፓኪስታን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ለንግድ ግንኙነት 78 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።