በመሬት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የጀመርነውን እርምጃ አጠናክረን እንቀጥላለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

18

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2015 በአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የጀመርነውን እርምጃ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለልማት የተሰጠን 90 ሄክታር መሬት ለረጅም ጊዜያት አጥረው ያቆዩና ወደ ልማት መግባት ያልቻሉ አካላትን የሊዝ ውላቸውን ማቋረጡን አስታውቋል።

መሬቱንም ወደ መሬት ባንክ ገቢ በማድረግ ለጨረታ እንዲቀርብ መወሰኑን ከንቲባ አዳነች በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

የተሰጣቸውን ውስን የሆነውን የመሬት ሀብት ወደ ስራ በማስገባት ሀገርንም ይሁን የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲያግዙ ብሎም ለብዙዎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ተበሎ የተሰጣቸውን መሬት ነው አጥረው ያቆዩት ብለዋል።

መሬቱን ወደ ልማት ከማስጋባት ይልቅ ጥቂቶች ምንም ሳይሰሩ ቦታውን እየሸጡ የሚከብሩበት ሁኔታ እንዳይቀጥል የጀመርነውን እርምጃ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡም የጀመርናቸውን የህግ የበላይነት እርምጃዎች እንዲደግፍ ጥሪ ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች የዜጎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም