በቅርቡ የፈነጠቀው የሰላም ሂደት ስር እንዲሰድ ሁሉም በጋራ መስራት አለበት - አገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በቅርቡ የፈነጠቀው የሰላም ሂደት ስር እንዲሰድ ሁሉም በጋራ መስራት አለበት - አገራዊ ምክክር ኮሚሽን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 12 ቀን 2015 በቅርቡ የፈነጠቀው የሰላም ሂደት ስር እንዲሰድ ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎቹን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሀገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባላት ጋር እየተወያየ ነው።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከተቋቋመ 8 ወራትን ያስቆጠረው ኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፉን እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ በክልልና በዞኖችና ቅርንጫፎችን የመክፈት፣ አወያይና አመቻቾችን ለይቶ ስልጠና የመስጠትና የአጀንዳ ልየታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ዓላማው ለኢትዮጵያዊያን ያለመግባባት መንስኤ የሆኑና ለአገር ዕድገት ሳንካ የሆኑ በመሰረታዊ ችግሮች ላይ በመካከር የጋራ አገራዊ መግባባት መፍጠር ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር መወያየቱን በማስታወስ።
የኢትዮጵያ ሀገር ሽማግሌዎች አገራዊ ስርዓትን ማስቀጠልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ እንዳላቸው ነው ፕሮፌሰር መስፍን የገለጹት።
ኮሚሽኑ የሕዝብና የአገር ጥቅም ካስቀደሙ አባቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በቅርቡ የፈነጠቀው የሰላም ሂደት በቀጣይነት ስር እንዲሰድ ሁሉም በጋራ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በውይይቱ መክፈቻ የኢትዮጵያ አገራዊ ኮሚሽኑ የእስካሁኑ ተግባራት እና ቀጣይ ስራዎች አስመልክቶ ለሀገር ሽማግሌዎቹ ገለጻ ተደርጓል።