ቀጥታ፡

የባህል አልባሳት ተፈላጊነት እየጨመረ ቢሆንም ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል አልተሰራበትም - አስተያየት ሰጪዎች

አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 የኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ተፈላጊነት እየጨመረ ቢሆንም ዘርፉ የሚፈለገውን ያህል እየተሰራበት እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ። ኢዜአ በሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳት ገበያ ላይ ያገኛቸውን ሸማቾችና ነጋዴዎችን ስለ ባህል አልባሳት እድገትና የገበያ ሁኔታ አነጋግሯል። አስተያየት ሰጪዎቹ የአገር ባህል አልባሳትን የሰርክ ልብስ ለማድረግና ወጣቶችም ከውጭ አገር ይልቅ የራሳቸውን እንዲመርጡ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ አይደለም ነው ያሉት። ወይዘሮ መቅደስ አበበ የተባሉት ሸማች ሙያተኞቹ በዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል እየሰሩበት እንዳልሆነና ወጣቱም የአገር ባህል አልባሳቱን እንዳልተጠቀመበት ይናገራሉ። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሙሉ ሸዋ አበበ ሁሌም የአገር ባህል አልባሳትን እንደሚመርጡ ገልጸው ከውጭ አገር ተመሳስሎ እየመጣ ያለው ልብስ 'ቢቀር' ብለዋል። ስዊድናዊቷ ሚስ አና ኒልሶን አርቲስት ናት፤ የአገር ባህል ልብስ ለመግዛት በሽሮ ሜዳ ተገኝታለች፤ ከአገሯ የመጣችው የኢትዮጵያን ባህል ለማጥናት ሲሆን በመስቀል ደመራ በዓል ለመታደም መጓጓቷንም ነግራናለች። አቶ በረከት አርጋው ከመቀሌና ያመጣቸውን አልባሳት ለነጋዴዎች እያስረከበ አግኝተን አነጋግረነዋል፤ አልባሳቶቻችን እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የክት ልብስ ሆነው ዘወትር እንዲለበሱ የዘርፉ ሙያተኞችና የመንግስትን ትኩረት እንደሚሻ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም