ቀጥታ፡

በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያለንን ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ፈጣሪነት ለሀገር ግንባታና ለስፖርት ዲፕሎማሲ ማዋል ይገባል-የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

ሰመራ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያለንን ዓለም አቀፍ ተጽእኖ ፈጣሪነት በሚመጥን ደረጃ ለሀገር ግንባታና ለስፖርት ዲፕሎማሲ ማዋል እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለዚህም ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታችንን በሚመጥን ደረጃ ፌዴሬሽኑ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል።

26ኛዉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ በአፋር ሰመራ ከተማ ተካሂዶ በትላንትናው ዕለት መጠናቀቁ ይታወሳል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳድር መስፍን ቸርነት 2014 ዓ.ም አትዮጵያ በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ስኬታማ ሆና ያሳለፈችበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ስኬት በዘርፉ የሚገኙ የስፖርቱ አመራሮችና አሰልጣኞች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎና ትብብር ውጤት መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

ውጤቱ ከነበርንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተስፋ ሰንቀን የገጠመንን ፈተና በጋራ እንድንሻገር አቅም የፈጠረ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ውጤታማነቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፌዴሬሽኑ ከመቼዉም ግዜ በላይ ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳትም የአትሌቲክስ ዘርፉ ውድድሮችን ከማሸነፍም ባለፈ የሀገር ገጽታና የኢኮኖሚ ግንባታ መስኩን በመደገፍ የማይተካ ሚናዉን መወጣት ይጠበቅበታልም ብለዋል።

በየውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ በአግባቡ እንዲውል ለማድረግ የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት።

አትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያላትን መልካም ስምና ውጤት በሚመጥን ደረጃ በአለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት ላይ ያለዉን ውስን ተሳትፎ ተገቢዉን ውክልና መያዝ እንዲቻል ፌዴሬሽኑ አቅዶ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

በተለይም በአትሌቲክሱ እንዳለን ጥሩ ስምና ውጤታማነት ከታላቁ ሩጫ ውድድር በተጨማሪ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ ውድድር በማዘጋጀት የስፖርት ዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወን ቀጣይ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም