ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሪፎርም ስራዎች የህግ የበላይነት ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ናቸው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሪፎርም ስራዎች የሕግ የበላይነት የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ባከበረ አግባብ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያስችሉ እንደሆኑ በተባበሩት መንግስት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ጽህፈት ቤት ተወካይ ማርሴል አክፖቮ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስዋና መስሪያ ቤትን እና  የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያን የጎበኙት በተባበሩት መንግስት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ጽህፈት ቤት ተወካይ ማርሴል አክፖቮ የተቋሙን ሪፎርም ስራዎች አድንቀዋል።

የወንጀል መከላከልና ወንጀል ምርመራ ስራዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስን አሰራሮች ከፖሊስ ተቋም የሚጠበቅ አሰራሮች ያማከሉ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉና ሰብዓዊ መብትን ያከበሩ ናቸው ብለዋል።

የህዝብ ደህንነትን ለማስጠበቅ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አሰባስብ ስርዓት ከመዘርጋቱ ባሻገር የሚሰበስባቸው መረጃዎች ለፍርድ ቤቶች ሁነኛ ማስረጃ ሆነው እንደሚቀርቡ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ተልዕኮ ተቀብለው የሚሰማሩ የፖሊስ መኮንኖችን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ትስስር መኖሩም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በቀላሉ ለመቅረፍ ያስችለዋል ብለዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የግለሰቦችን ግላዊ መብት ያከበሩ መሆን እንዳለባቸው የገለጹት ኃላፊው፤ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ያማከሉ አሰራሮችን በቀጣይነት ማጠናከር አለበት ብለዋል።

በሌላ በኩል የፍትህ ስርዓቱ ወሳኝ አካል የሆነው የወንጀል ምርመራ ክፍል የተዘረጉ አሰራሮችም በዘርፉ የሚጠበቁ ፖሊሳዊ ኃላፊነቶችን የጠበቁ እንደሆኑ ትዝብታቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገነቡ አሰራሮች አንድ ተጠርጣሪ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስኪባል ድረስ ነጻ ሆኖ የመገመት እና ሰብዓዊ መብቱም የመጠበቅ የሚሉ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ እንደሆኑ አንስተዋል።

የወንጀል ምርመራ ክፍሉ ተጠርጣሪው ግለሰብና መርማሪው የሚነጋገሩበት ክፍል ተጠርጣሪው በራስ መተማመኑ ሳይጓደል፣ ለአካላዊ ጥቃት ሳይጋለጥ እና የሙስና ስጋት ሳይኖርበት የሚካሄድ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተጠርጣሪውን ሰብዓዊ መብት በጠበቀ አግባብ እንዲከውንም ብቻ ሳይሆን መርማሪም ሙሉ ኃላፊነት ተሰምቶት ምርመራውን በአግባቡ እንዲያከናውን የሚያግዝ እንደሆነ አንስተዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስትና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የጀመሩት ሪፎርም ለመሰረታዊ የፖሊስ አገልግሎቶች በአግባቡ መከወንና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የታከለበት በመሆኑ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይህ አሰራር በህግ የበላይነት ማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ህዝቡ በተቋሙ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው እና የፍትህ ሥርዓቱ ሳይጓደል እንዲፈፀም ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ተቋሙ የጀመራቸው ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ክፍተቶችን በመማር ማረምን፣ የፖሊስ መኮንኖችን አቅም ግንባታን ማጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

በፖሊስ ተቋም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች በዚህ አግባብ ተጠናክረው ከቀጠሉ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የልህቀት ማዕከል እና ምሳሌ እንደምትሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የጀመራቸው የለውጥ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸውም የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ድጋፉን እንደሚያጠናከር አረጋገጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም