የጥራሪ ወንዝ ድልድይ የመልሶ ግንባታ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የጥራሪ ወንዝ ድልድይ የመልሶ ግንባታ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
ሰቆጣ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 ከሰቆጣ - ኮረም መንገድ የሚያገናኘው የጥራሪ ወንዝ ድልድይ የመልሶ ግንባታ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በዛሬው እለት ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይና ስትራክቸር ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ዘለቀ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የጥራሪ ወንዝ ድልድይ የመልሶ ግንባታ ስራ 24 ሰዓት ተካሂዶ በአጭር ጊዜ መልሶ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተደርጓል።
የመንገዶች አስተዳደር ለድልድዩ ስራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በሙሉ ወደ ቦታው ማጓጓዝ በመቻሉ የመልሶ ግንባታው ስራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
የድልድዩ መልሶ ግንባታ ህዳር 03 ቀን 2015 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በተቀናጀ መንገድ በተደረገ ርብርብ በስምንት ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ጠቁመዋል።
ለመልሶ ግንባታው ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ገልጸው፤ ድልድዩ መልሶ ለአገልግሎት መብቃቱ የአካባቢውን እንቅስቃሴ በማሳለጥ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይ ባለሙያ አቶ ዋሜ ጣባ በበኩላቸው ድልድዩ ካሁን ቀደም የነበረው ጭነት የመሸከም አቅም እንዲያድግ ተደርጎ መገንባቱን ጠቁመዋል።
በዚህም የድልድዩ 20 ቶን ክብደት የመሸከም አቅም ወደ 40 ቶን ከፍ እንዲል ተደርጎ ተሻሽሎ መሰራቱን ተናግረዋል።
የጥራሪ ወንዝ ድልድይ 42 ሜትር ርዝመት 4 ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር ስፋት እንዳለውም ባለሙያው አስታውቀዋል።
የአገር መከላከያ ሰራዊት የሎደርና ሌሎች እገዛ ማድረጉ የጥገና ስራውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ማገዙን ገልፀዋል።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋንታይቱ ካሴ እንዳሉት፤ የጥራሪ ወንዝ ድልድይ ከጥቅም ውጭ ሆኖ በቆየባቸው ወራቶች ህዝቡ ከእንግልትና ስቃይ ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ጫና ተዳርጎ ቆይቷል።
ድልድዩን ለመጠገን 24 ሰዓት ለሰሩ ባለሙያዎችና ለአገር መከላከያ ሰራዊት ምስጋና አቅርበዋል።
የጥራሪ ወንዝ ድልድይ መልሶ መገንባትም ሰቆጣ-ኮረም-አላማጣ-ወልዲያ-ደሴ ድረስ የሚወስደውን መንገድ የሚያስተሳስር መሆኑ ይታወቃል።