ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ለጎረቤት ሀገራት እየሰጠ ያለው ነፃ የትምህርት ዕድል ለቀጠናዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ፋይዳ አለው - ተማሪዎች

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጎሮቤት ሀገራት እየሰጠ ያለው ነፃ የትምህርት ዕድል ለቀጠናዊ ትስስር መጠናከር ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ዕድሉን ያገኙ ተማሪዎች ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው አሁኑ ላይ 56 የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎችን በውሃ ምህንድስና እና በሌሎች የትምህርት ዘርፎች በነጻ ተቀብሎ እያሰለጠነ እንደሚገኝም ተገልጿል።

ዩኒቨርሲቲዉ ከሰው ሀብት ስልጠናው ባሻገር በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

በዩኒቨርሲቲው በጤናዉ ዘርፍ የሁለተኛ ድግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘዉ ደቡብ ሱዳናዊው ተማሪ ሬይክ ጋትከክ የኢትዮጵያ መንግስት ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች ባመቻቸው ነፃ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ በመሆኑ መደሰቱን ገልጿል።

"ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት እናት ናት" ያለው ተማሪው፤ በተለይም ለሀገራቱ ነጻ መውጣት ካደረገችው ተጋድሎ አንስታ ዛሬም ድረስ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት በግንባር ቀደምነት ሃላፊነቷን ሳታቋርጥ እየተወጣች መገኘቷን ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት በሰው ሀብት ልማት እያደረገች ያለው አስተዋጽኦ በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የተናገረው።

ዩኒቨርሲቲው ለአፍሪካ ሀገራት የሰው ሃይል ልማት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ያደነቀው ተማሪው፤ በዚሁ ዕድል መነሻነት ሰሞኑን የደቡብ ሱዳን ውሃና መስኖ ልማት ሚኒስትር በመሆን የተሾሙትን የቅርብ ጓደኛውን በማሳያነት ጠቅሷል።

ነፃ የትምህርት ዕድል መሰጠቱ ለሀገራችን ዕድገት ተገቢዉው አስተዋጽኦ እንድናበረክት ጉልህ ድርሻ አለዉ ያለው ደግሞ በውሃ ምህንድስና ዘርፍ የ2ኛ ድግሪውን እየተከታተለ የሚገኘዉ የሶማሊላንድ ተማሪ ያሲን አብዱላሂ ነዉ።

ይህ ዕድል ከትምህርቱም በላይ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትስስር እና የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ሰላማዊና ጤናማ እንዲሆን ያግዛል ሲልም ተናግሯል።

ዩኒቨርሲቲው  በአሁኑ ሰዓት 56 የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎችን ተቀብሎ በተለያየ የሙያ መስክ እያሰለጠነ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል 33ቱ በመጀመሪያ ድግሪ መሆናቸውን ገልጸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን አመላክተዋል ።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት እና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትስስር የሚረዱ በርካታ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸው ከዚህ ውስጥ አንዱ በትምህርት ዘርፍ የነጻ ትምህርት ዕድል በመስጠት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው በውሃው ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ለሀገራችን ብሎም ለዓለም ከፍተኛ ምሁራንን በማፍራትና በምርምር ስራ የበኩሉን እየተወጣ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ሰዓት በዘርፉ አስር የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን በመክፈት ተማሪዎችን እያስመረቀ ይገኛል  ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሰባት የምርምር ማዕከላት በመክፈትና የተለያዩ የውሃ ምህንድስና ቤተ ሙከራዎችን በማቋቋም ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በውሃ ምህንድስና ዘርፍ በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ1979 ዓ.ም የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሚል ስያሜ የተመሠረተ ሲሆን ሌሎች የትምህርት ክፍሎችን በማካተት በ1996 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ማደጉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም