የመከላከያ ሚኒስቴር መንግስትን ወክለው በሰላም ስምምነቱ ለተሳተፉ አካላት እውቅና እና ሽልማት አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሚኒስቴር መንግስትን ወክለው በሰላም ስምምነቱ ለተሳተፉ አካላት እውቅና እና ሽልማት አበረከተ
አዲስ አበባ ህዳር 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) የመከላከያ ሚኒስቴር መንግስትን ወክለው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያና በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ለተሳተፉ አካላት እውቅና እና ሽልማት አበረከተ፡፡
የእውቅና እና ሽልማት ስነ-ስርዓቱ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
ዶክተር አብርሃም በዚሁ ጊዜ፤ መንግስትን ወክለው በሰላም ሂደቱ የተሳተፉ አካላት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
የሰላም ስምምነቱ በስኬት እንዲጠናቀቅና ለመላ ኢትዮጵያውያን በተለይም በግጭት ቀጣናው ውስጥ ለነበሩ ዜጎች ተስፋን የፈነጠቀ በመሆኑ፤ ለዚህ ስኬት የላቀ ሚና የተወጡ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የተገኘውን ሰላም በተሟላ መልኩ መሬት ላይ በማውረድ ህዝብ የተሰማውን እፎይታ ዘላቂ የማድረግ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።
መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነትና ዘላቂነት ቁርጠኛ መሆኑን ያረጋገጡት ሚነስትሩ፤ ሆኖም የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚሰሩ የግጭት ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊቱ አገሩን የሚወድና ሰላምን የሚያስቀድም ጀግና ሰራዊት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካና ኬኒያ የተካሄደው የሰላም ስምምነትም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባስጠበቀ መልኩ መከናወኑንም አንስተዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ በጥሩ ሁኔታ ተካሂዶ የጋራ መግባባት የተፈጠረበት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡
የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፤ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ሰላም ፈላጊ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ መንግስትም ይህንን የኢትዮጵያን ጽኑ አቋም በተደጋጋሚ አሳይቷል ነው ያሉት።
ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም ንግግሩ እንዲሳካ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ስምምነቱም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባረጋገጠ መልኩ መካሄዱን ጠቅሰዋል።
የፌደራል መንግስትና ህወሃት በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት በደቡብ አፍርካ ፕሪቶሪያ ለ10 ቀናት የሰላም ንግግር ካካሄዱ በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የሰላም ስምምነት ተፈራረመዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የህወሃት ታጣቂዎች አመራሮችም በኬንያ ናይሮቢ የሰላም ስምምነቱን የማስፈጸሚያ እቅድና የህወሃት ታጣቂዎች የትጥቅ አፈታት ሂደት ላይ ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም ተስማምተዋል።