ቀጥታ፡

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከተ.መ.ድ የፍልሰት ተወካይ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ  መስከረም 16/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ የዓለምአቀፍ ፍልሰት ልዩ ተወካይ ሎይስ አርቦር ጋር ተወያዩ፡፡ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ከልዩ ተወካይ አርቦር  ጋር በተወያዩበት ወቅት በስደት ምንጮችና መዳረሻ ቦታዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ተወስቷል። ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 73ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተለያዩ ዓለምአቀፍ አንኳር ጉዳዮች ላይ እየተወያየ ይገኛል። የመንግሥታቱ ድርጅት ''ለሁሉም ጥቅም ያለው፤ ለሠላም፣ ለፍትኃዊና ለዘላቂ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ አመራርና የጋራ ኃላፊነት" በሚል መሪ ሀሳብ ከሚያካሂደው ስብሰባ ጎን ለጎን የተለያዩ መድረኮች ተከፍተው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል። በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑክም ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገሮችና ከዓለምአቀፍ ተቋማት ተወካዮች ጋር እየተወያዩ ናቸው። ቀደም ብሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሽብርተኝነት መከላከል ጽህፈት ቤት ረዳት ጸሀፊ ቭላድሚር ቮሮንኮቭ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። ፕሮፌሰር አፈወርቅ በኢትዮጵያ የስደተኞች ምንጭ፣ መተላለፊያና መዳረሻነት ዙሪያ ከዋና ፀሀፊው የዓለምአቀፍ ፍልሰት ተወካይ ጋር ትናንተ ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉት ማሻሻያዎች በቀጣናው ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ፍልሰት ላይ ስለሚኖራቸው ተፅዕኖም ሀሳብ መለዋወጣቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የላከው የፕሬስ መግለጫ ያመለክታል። ታህሳስ 1 እና 2 ቀን 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ማራካሽ  ዓለምአቀፋዊ የፍልሰት ስምምነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሊካሄድ ስለታሰበው  የበይነ  መንግስታት ጉባዔም አንሰተው መክረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በ73ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኒውዮርክ የገቡት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም