ቀጥታ፡

በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 3ኛውን የኢትዮጵያ ቀን በአቡዳቢ ከተማ አከበሩ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሶስተኛውን "የኢትዮጵያ ቀን" በአቡዳቢ ከተማ አክብሩ።

በበዓሉ ላይም በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በሀገራቸው ልማት ጉዳይ ላይ ሁሌም ንቁ ተሳታፊ በመሆናቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በ"ጉዞ ወደ ሀገር ቤት" እና "ከኢድ እስከ ኢድ" ጥሪዎች ወቅት ያደረጉት ተሳትፎ ከፍ ያለ እንደነበረም ጠቅሰዋል።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ቀን በዓልም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት በታሰረበትና በመላው ሀገራችን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ተስፋ በታየበት ወቅት ለየት ባለ ሁኔታ እየተከበረ ነው ብለዋል።

ይህ ሰላም ዘላቂ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ዜጋዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸውም አምባሳደር ሱሌማን ገልጸዋል።

በዓሉ የእግር ኳስ ውድድር፣ የሙዚቃ ዝግጅት፣ ፋሽን ሾው፣ ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢ የተዘጋጀ የሎተሪ ዕጣ የማውጣት ሁነቶችን ያካተተ እንደነበረ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም